የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 2016 ዓ.ም. በሚያካሂደው ምርጫ የሚወዳደሩ ዕጩዎች በድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ የሚኖራቸውን ቅደም ተከተል የሚወሥነውን የዕጣ ማውጣት ሥነ-ሥርዓት አካሄደ ::
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ6ኛው ዙር የጠቅላላ እና የድጋሚ ምርጫ ባልተካሄደባቸው የቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ የአፋር፣ የሶማሌ እና የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሚያካሂደው ምርጫ የተለያዩ የቅድመ-ምርጫ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑ ይታወቃል። ከነዚህም ተግባራት አንዱ የዕጩዎች ምዝገባ ሲሆን፤ በትላንትናው ዕለት ማለትም ግንቦት 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የተመዘገቡ ዕጩዎችን በድምፅ መስጫ ወረቀቱ ላይ የሚኖራቸውን የአደራደር ቅደም ተከተል የሚወሥነውን የዕጣ ማውጣት ሥነ-ሥርዓት አካሂዷል።
በዚህ የዕጣ ማውጣት ሥነ-ሥርዓት ላይ የቦርዱ ዋና ሰብሳቢን ጨምሮ ሁሉም የቦርድ አመራር አባላትና በምርጫው ላይ የሚሣተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዩች የተገኙ ሲሆን፤ ሥነ-ሥርዓቱም የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ተከፍቷል።