ለመራጮች ስለሚሰጡ የምርጫ መረጃዎች
አንድ መራጭ በመራጭነት ተሳትፎ የሚፈልገውን ፓርቲ ወይም እጩ ተወዳዳሪ ለመምረጥ የሚችለው በቅድሚያ በመራጭነት ሲመዘገብ ብቻ ነው፡፡ በመራጭነት ሳይመዘገብ ቀርቶ በድምፅ መስጫው እለት መራጭ ሆኖ መቅረብ አይችልም፡፡ ስለሆነም ቦርዱ ስለመራጮች ምዝገባ መጀመር በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ሲገልጽ በመከታተልና በመመዝገብ የመራጭነትን መብትን በእጅ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡
የመራጮች ምዝገባ ቅድመ ሁኔታ
በማንኛውም ምርጫ ለመሳተፍ አስቀድሞ በመራጭነት መመዝገብ ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ አንድን ሰው በመራጭነት ለመመዝገብ የሚያበቁት መስፈርቶችና የሚያስፈልጉት ሰነዶች በምርጫ ህግና እንደ አስፈላጊነቱም በምርጫ ቦርድ በሚወጡ ዝርዝር መመርያዎች ይቀመጣሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ መስፈርቶች ተገቢና አስፈላጊ በሆነ መጠን ብቻ እንጂ አንድን ሰው ያለ አግባብ ከመራጭነት የሚያገሉ አይሆኑም፡፡
የመራጮች ምዝገባ የሚከናወነው በምርጫው ዓይነት ላይ ተመስርቶ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሚያወጣው የመራጮች ምዝገባ የጊዜ ሰሌዳ አማካኝነት ሲሆን የምዝገባ ቦታውም መራጮች በሚኖሩበት ቀበሌ በሚቋቋም የምርጫ ጣቢያ ብቻ ነው፡፡ ሆኖም በአርብቶአደር አካባቢዎች አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ተንቀሳቃሽ የምርጫ ጣቢያ በማቋቋም የመራጮችን ምዝገባ ማከናወን ይቻላል፡፡ አንድ ሰው ለመራጭነት በአንድ የምርጫ ጣቢያ መመዝገብ የሚችለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው! እያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ የራሱ የሆነ የመራጮች መዝገብ ይኖረዋል፡፡
በምርጫ ህጉ አንቀጽ 18 አዋጅ ቁ. 1162/2011 መሠረት አንድ ሰው በመራጭነት መመዝገብ የሚችለው፡-
- ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከሆነ፣
- በምዝገባው እለት እድሜው 18 ዓመትና ከዚያ በላይ ከሆነ እና
- ለምዝገባ በቀረበበት የምርጫ ክልል ቢያንስ ለ6 ወራት የኖረ ከሆነ ብቻ ነው፡፡
ከላይ በዝርዝር የተቀመጠው እንደተጠበቀ ሆኖ በአዕምሮ ህመም ምክንያት የመወሰን አቅም የሌለው መሆኑ ስልጣን ባለው አካል ወይም በበቂ ማስረጃ የተረጋገጠበት ሰው እንዲሁም የመምረጥ መብቱ በህግ ወይም አግባብ ባለው ህግ መሠረት በፍርድ ቤት ውሳኔ የተገደበበት ሰው በመራጭነት ሊመዘገቡ አይችሉም፡፡
የመራጮች ምዝገባን በተመለከተ ሁለት ሊታወሱ የሚገባቸው ጉዳዮች፦
- የመራጮች ምዝገባ ሊከናወን የሚችለው ቦርዱ በሚያወጣው ውስን የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ ብቻ ነው፡፡
- ቀደም ሲል እንደተገለጸው ለአርብቶአደር አከባቢዎች በተለየ ሁኔታ ካልተወሰነ በስተቀር ምዝገባው የሚከናወነው መራጮች በሚኖሩበት ቀበሌ በሚቋቋም የምርጫ ጣቢያ ብቻ ነው፡፡
አንድ ሰው ለመራጭነት ለመመዝገብ ወደ ምርጫ ጣቢያ በሚመጣበት ጊዜ የሚከተሉትን ሰነዶች መያዙን ማረጋገጥ ይኖርበታል፦
- ተመዝጋቢው በሚኖርበት የምርጫ ጣቢያ ማንነቱን የሚገልፅ የቀበሌ መታወቂያ ካርድ ወይም ፓስፖርት (ያልታደሰም ቢሆን)፣
- የቀበሌ መታወቂያ ካርድ ማቅረብ ካልተቻለ በቅርቡ ፎቶግራፍ ተደርጎበት የተሰጠ እንደ የመንጃ ፈቃድ፣ የመኖሪያ የምስክር ወረቀት፣ ከውትድርና የተገለለበት ሰነድ፣ የትምህርት ቤት መታወቂያ የመሳሰሉ የመለያ ማስረጃዎች፣
- ከላይ የተዘረዘሩት ማስረጃዎች በማይኖሩበት ወቅት መዝጋቢዎች መራጩን ለይተው የሚያውቁት ከሆነ ወይም በገጠር አካባቢ ሲሆን በባህላዊና ልማዳዊ ዘዴ ተመዝጋቢውን ለመለየት የሚቻልበት ሁኔታ ካለ እንዲሁም የምርጫ ጣቢያው በተቋቋመበት ቀበሌ ኗሪ የሆኑ ለረዥም ጊዜ መኖራቸው የተረጋገጠ ሦስት ግለሰቦች ነዋሪዎች በሚሰጡት ምስክርነት ማስረጃ አልባውን ተመዝጋቢ ለመለየት ከተቻለ ቃለ ጉባኤ ተይዞ ምዝገባው ይከናወናል፡፡
በተለያየ ምክንያት ራሳቸውን ችለው መመዝገብ የማይችሉ ሰዎች በረዳቶቻቸው አማካኝነት በአካል ተገኝተው መመዝገብ ይኖርባቸዋል፡፡
በመራጮች ምዝገባ ሂደት ስለሚነሱ ክርክሮች
የመራጮች ምዝገባን የሚመለከት ማናቸውም ተቃውሞ በማንኛውም ሰው ወይም የፖለቲካ ድርጅት ለምርጫ ጣቢያው አቤቱታ ሰሚ ኮሚቴ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ማለት በክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት፣ በምርጫ ክልል እና በምርጫ ጣቢያ ደረጃ ለሚነሱ ቅሬታዎች አስተዳደራዊ ውሳኔ የሚሰጥ በምርጫ ህጉ መሠረት ለምርጫ ወቅት የሚቋቋም ኮሚቴ ነው፡፡ በምርጫ ህጉ ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው ማንኛውም ሰው በመራጭነት ከመመዝገብ የተከለከለ እንደሆነ ወይም በመራጭነት መመዝገብ የሌለበት ሰው ወይም መብት የሌለው ሰው ያለአግባብ ተመዝቧል የሚል ሰው ወይም የፖለቲካ ድርጅት ተቃውሞውን ለምርጫ ጣቢያ አቤቱታ ሰሚ ኮሚቴ ማቅረብና ውሳኔ የማግኘት መብት አለው፡፡ በዚህ መሠረት የሚቀርብ አቤቱታ የማቅረቢያ ጊዜ ከመራጮች የምዝገባ ቀን ጀምሮ የመራጮች መዝገብ ለሕዝብ ይፋ የሚሆንበት ጊዜ እስከሚያልቅ ድረስ ይሆናል፡፡
አንድ የምርጫ ጣቢያ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ የቀረበለትን አቤቱታ መርምሮ በ5 ቀናት ውስጥ ውሳኔውን በጽሑፍ ለቅሬታ አቅራቢው ያቀርባል፡፡ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴው በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ውሳኔ ካልሰጠ ወይም ቅሬታ አቅራቢው በተሰጠው ውሳኔ ያልተስማማ እንደሆነ አቤቱታ አቅራቢው ለምርጫ ክልሉ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ በ5 ቀናት ውስጥ አቤቱታ በማቅረብ ውሳኔ የማግኘት መብት አለው፡፡ ምርጫ ክልሉ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ በ5 ቀናት ውስጥ ውሳኔ ካልሰጠ ቅሬታ ወይም ቅሬታ አቅራቢው በተሰጠው ውሳኔ ያልተስማማ እንደሆነ በ5 ቀናት ውስጥ ሥልጣን ላለው በየደረጃው ላሉ የፌደራል ወይም የክልል ፍርድ ቤት ጉዳዩ እንዲታይለት አቤቱታ የማቅረብ መብት አለው፡፡ አቤቱታ የቀረበለት ፍርድ ቤትም የቀረበለትን አቤቱታ ለመወሰን የሚያሰፈልጉ ማስረጃዎችን አስቀርቦ በመመርመር ውሳኔ ይሰጣል፡፡