ድምፅ አሰጣጥ
በመራጮች ምዝገባ ወቅት ከተመዘገቡ ዜጎች በኃላ በቦርዱ በተወሰነው የድምፅ መስጫ ቀን የተመዘገቡበት የምርጫ ጣቢያ በመሄድ ድምፅ ይሰጣሉ፡፡ የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ የሚከተለውን ይመስላል፡፡
የድምፅ አሰጣጥ ሂደት
- የድምፅ መስጠት ሂደት በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች በተመሳሳይ ሰዓት ይጀመራል፡፡
- በዕለቱም መራጮች በምርጫ ጣቢያው ከጠዋቱ 12፡00 ጀምሮ እከስ ምሽት 12፡00 ሰዓት ድረስ በመገኘት ድምፃቸውን መስጠት ይችላሉ፡፡ በነዚህ ሰዓታት ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ያልተቋረጠ የድምፅ መስጠት ተግባር ይከናወናል፡፡
- ማንኛውም መራጭ ዜጋ በምርጫ ጣቢያው በአካል በመገኘት በሙሉ ነፃነት ድምፅ ይሰጣል፡፡
- ማንኛውም ዜጋ ድምፅ መስጫ ወረቀቱ ላይ ከሚመርጠው እጩ አጠገብ ባለው ቦታ ማንኛውንም (ኤክስ፣ ራይት ወይም የጣት አሻራ) ምልክት በማድረግ ድምፁን ይሰጣል፡፡
- ማንኛውም ድምፅ የሚሰጠው በሚስጥር ነው፡፡ ድምፅ ለመስጠት እገዛ የሚያስፈልጋቸው ድምፅ ሰጪ ዜጎች ድጋፍ የሚሰጣቸውን ሰው ይዘው የሚስጥር ድምፅ መስጫ ውስጥ መገኘት ይችላሉ፡፡ ድጋፍ ሰጪው መብቱ በህግ ያልተገደበ መሆን አለበት፡፡
- ማንኛውም መራጭ ድምፅ መስጠት የሚችለው፦
- በመራጭነት በተመዘገበበት የምርጫ ጣቢያ ላይ፣
- የመራጮች መታወቂያ ካርድ ሲኖረው፣
- በመራጮች መዝገብ ላይ ሰፍሮ ሲገኝ፣
- እንዲሁም ድምፅ ያልሰጠ መሆኑ ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡
- ማንኛውም መራጭ ድምፅ ለመስጠት በተገኘበት ምርጫ ጣቢያ ላይ ይዞ የተገኘውን የማንነት መግለጫ ሰነዶች በጣቢያው ላይ በሚገኙ የምርጫ አስፈጻሚዎች ድምፅ እንዲሰጥ መፍቀዳቸውን ማጣራት ይችላሉ፡፡
- አካል ጉዳተኞች፣ አረጋዊያን፣ ህጻናትን የያዙ ወላጆች እና ነፍሰ ጡሮች በምዝገባም ሆነ በድምፅ አሰጣጥ ሂደት ቅድሚያ ይሰጣቸዋል፡፡
- ድምፅ የተሰጠባቸው ወረቀቶች ከሚከተሉት በአንዱ ምክንያት ዋጋ አልባ ሊሆኑ ይችላሉ፦
- የመራጩ ማንነት በስም የተገለፀ ከሆነ፣
- ለምክር ቤቱ መምረጥ ከሚቻለው እጩዎች ቁጥር በላይ ምልክት የተደረገበት ከሆነ፣
- መራጩ ማንን እንደመረጠ መለየት የሚያስቸግር ከሆነ፣
- ሕጋዊ የድምፅ መስጫ ወረቀት ያልሆነ ወይም በምርጫ ጣቢያው ያልተሰራጨ የድምፅ መስጫ ወረቀት ሆኖ ከተገኘ፡፡
በድምፅ መስጫ እለት ሊከበሩ የሚገባቸው ስነ-ምግባር መርሆዎች
- ማንኛውም ሰው በምርጫ ጣቢያው 200 ሜትር ዙሪያ ክልል ውስጥ በስካር መንፈስ ውስጥ ሆኖ፣ የጦር መሣሪያ በመያዝ ወይም በሌላ በማናቸውም ፀጥታን በሚያደፈርስ አኳኋን መገኘት የለበትም፡፡
- ማንኛውም ድምፅ ሰጪ ያልሆነ ሰው ያለእውቅና መታወቂያ ወደ ምርጫ ጣቢያው በመግባት ወይም በምርጫ ጣቢያው ግቢ ውስጥም ሆነ ውጭ የምርጫውን እንቅስቃሴ ማወክ ወይም ማደናቀፍ የለበትም፡፡
- ድምፅ ሰጪው ድምፅ ከሰጠ በኋላ ምርጫ ጣቢያውን እና ከባቢውን ለቅቆ መሄድ ይኖርበታል፡፡