በምርጫ ሥርዓት፣ የድምፅ አሰጣጥ ከመጀመሩ በፊት ከሚደረገው የቅድመ ምርጫ ዝግጅት ጀምሮ ውጤቱ እስኪታወቅና ይፋ ሆኖ ለአሸናፊዎቹ የአሸናፊነት ማረጋገጫ እስከሚሰጥበት እንዲሁ ቅሬታ ካለ ቅሬታ መስማት ሂደቱ የሚከናወንበት የድህረ ምርጫ ክንውን ድረስ ያለውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ የሚያካትተው የምርጫ ሒደት፣ የምርጫ ዑደት ይባላል፡፡ በመሆኑም፣ የምርጫ ዑደት ሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ያቀፈ ነው፡፡ እነርሱም፣ ቅድመ ምርጫ፣ የምርጫ ጊዜ እና ድህረ ምርጫ ናቸው፡፡

ቅድመ ምርጫ

ቅድመ ምርጫ፣ ከድምፅ መስጫ ቀን በፊት ያለው ጊዜ ሲሆን፣ አብዛኛው የምርጫ እንቅስቃሴ የሚከናወንበት ወቅት ነው፡፡ በቅድመ ምርጫ ወቅት፥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝግጅት እና ምዝገባ፣ የህግ ማእቀፍ ዝግጅት፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ፣ ሥልጠና እና ምደባ፣ የምርጫ ክልልን የማካለል ሥራዎች፣ የመራጮች ምዝገባ፣ የፆታ አሳታፊነት፣ የብዙሃን ማኅበራት አሳታፊነት፣ የሥነ ዜጋ እና መራጮች ትምህርት፣ የምርጫ ጣቢያ አደረጃጀት፣ የዕጩዎች ምዝገባ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ፣ የብዙሃን መገናኛዎች የሥራ እንቅስቃሴዎች በስፋት እና በጥልቀት የሚሠሩበት ወቅት ነው፡፡ ይህ ወቅት በምርጫ አስፈጻሚው ተቋም እንዲሁም በሌሎች ባለድርሻ አካላት መጠነ ሰፊ ዝግጅት የሚያደርጉበት ጊዜ ነው፡፡

 

የምርጫ-ዑደት

የምርጫ ወቅት

በምርጫ ዑደት (Electoral cycle) መሠረት፣ በምርጫ ወቅት፣ በርካታ ወሳኝ ተግባራት የሚከናወኑበት ነው፡፡ የድምፅ አሰጣጥ፣ ቆጠራ፣ ውጤት አገላለጽ እና ማረጋገጥ፣ እንዲሁም፣ የቅሬታ አቀራረብ እና አፈታት በዚህ ምዕራፍ የሚካተቱ ተግባራት ናቸው፡፡

ድኅረ ምርጫ 

የድህረ ምርጫ፣ የተሰጠው ድምጽ ቆጠራ ተከናውኖ የምርጫ ውጤት ይፋ ከሆነ በኋላ ያለው ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ወቅት፣ የድህረ ምርጫ ግምገማ፣ በህጋዊ ማእቀፎች መሠረት የምርጫ ክልል ማካለል እና የተቋሙን ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ዝግጅት እና የመሳሰሉትን ሰፊ ሥራዎችን ያካትታል፡፡ ስለምርጫ ዑደት በዝርዝር ለመረዳት የሚከተለውን ፋይል ማንበብ ይችላሉ፡፡  

ተጨማሪ ያንብቡ