የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የወጣቶች የክርክር መድረክ በአዲስ አበባ ከተማ አካሔደ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ወጣቶች በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እና ሀገራዊ ኃላፊነት ጉዳዩች ዙሪያ በዕዉቀት የተደገፈ መረጃ እንዲኖራቸዉ በማስቻል ረገድ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የስነ ዜጋ እና መራጮች ትምህርት ሥራ ክፍል ሴፍ ላይት ኢኒሼቲቭ ከተባለ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ጋር በመተባበር የወጣቶች የማጠቃለያ የክርክር መድረክ በአዲስ አበባ ከተማ አካሒዷል፡፡
ክርክሩ በሴፍ ላይት ኢኒሼቲቭ ዋና መስሪያ ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ ዉስጥ የተካሄደ ሲሆን ቀደም ሲል በጅማ እና ቢሾፍቱ ከተሞች ላይ ሲካሔድ ለቆየዉ የክርክር መድረክ ማጠቃለያ ፕሮግራም ነዉ፡፡ ክርክሩ የተካሔደዉ በዩኒቨርሲቲ እና በሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መካከል ሲሆን ‘የፖለቲካ ፓርቲዎች ከኢኮኖሚ ፖሊሲ እና ከትምህርት ፖሊሲ የትኛዉ ላይ ትኩረት ቢያደርጉ በህዝቡ ተመራጭ ያደርጋቸዋል?’ በሚል ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ነዉ፡፡