የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአካል ጉዳተኞች አካታችነት ላይ ሥልጠና አካሄደ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቦርዱ ሥራ ክፍል ኃላፊዎችና ከፍተኛ ባለሞያዎች የተሣተፉበትን ሥልጠና መርኅ-ግብር መስከረም 8 እና መስከረም 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሁለት ቀናት የአካል ጉዳተኞች አካታችነት ላይ ሥልጠና አካሄደ። ስልጠናዉን በንግግር ያስጀመሩት የቦርድ አመራር አባል የሆኑት ፍቅሬ ገ/ሕይወት ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም ቦርዱ በተለይም በምርጫ ወቅት ትኩረት ሠጥቶ ከሚሠራባቸው ጉዳዮች ውስጥ የአካል ጉዳተኞች አካታችነት ከዋነኞቹ እንደ አንዱ የሚጠቀስ መሆኑን፤ ይኽም ሥልጠና ቦርዱ ለጉዳዩ የሚሰጠው ትኩረት በምርጫ ወቅት ብቻ የተገደበ ላለመሆኑ ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል። አመራሩ፤ በተጨማሪም አካል ጉዳተኛ የማኅበረሰብ ክፍሎች በምርጫ ወቅት በበቂ ላለመሣተፋቸው ምን ዓይነት ተግዳሮቶች አሉባቸው የሚለውን በመለየት የመፍትሔውም አካል መሆን እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።