የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በወላይታ ዞን የሚካሄደውን የድጋሚ ሕዝበ ውሣኔን ምርጫ በተመለከተ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጋር ምክክር አካሄደ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በወላይታ ዞን የሚደረገውን የድጋሚ ሕዝበ ውሣኔ ምርጫ አስመልክቶ በመራጮች ትምህርትና በምርጫ መታዘብ ላይ ከተሠማሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እንዲሁም በሰብዓዊ መብት ክትትል ተግባራት ላይ ከተሠማራው ከኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጋር ሚያዚያ 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ውይይት አካሄደ። የውይይት መድረኩ የቦርድ አመራር አባል የሆኑት ብዙወርቅ ከተተ ባደረጉት ንግግር የተከፈተ ሲሆን፤ በንግግራቸውም የድጋሚ ምርጫ ማካሄድ ያስፈለገበት ዋና ዋና ምክንያቶች አብራርተዋል። በተጨማሪም የመራጮች ትምህርት በሚሰጥበት ወቅት ምን ምን ጉዳዮች መካተት እንዳለባቸው እና ልዩ ድጋፍ የሚሹ የማኅበረሰቡን ክፍሎች ተደራሽ ሊደረጉ የሚችሉበትን አግባብነትና አማራጮች አስረድተዋል።