የትግራይ ክልል ምክር ቤት የክልል ምክር ቤት ምርጫ እንዲፈጸምለት ለቦርዱ ያቀረበውን ጥያቄ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ መግለጫ
ሰኔ 17 ቀን 2012 ዓ.ም
የትግራይ ክልል ምክር ቤት “ኮቪድ 19ኝን እየተከላከለ 6ኛውን ዙር ምርጫ ለማካሄድ የወሰነ በመሆኑ የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በሚያዘው መሰረት ቦርዱ ውሳኔውን ተቀብሎ ምርጫውን እንዲያስፈፅም፣ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስፈልግ የሰው ሃይልና ሎጂስቲክስ ዝግጅት እንዲያደርግ እና ውሳኔውን ለምክር ቤቱ እንዲያሳውቀን” ሲል ጥያቄ አቅርቧል፡፡ በመላ አገሪቱ በፌዴራልም ሆነ በክልሎች የሚደረጉ ምርጫዎችን የማስፈፀም ስልጣን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መሆኑ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 102 (1) ላይ ተደንግጓል ፡፡ህገ መንግስቱን መሰረት አድርጎ የቦርዱን ስልጣን እና ሀላፊነት የወሰነው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1133/2011 በአንቀጽ 7.1 ይህ የቦርዱ ስልጣን በሀገሪቱ ውስጥ የሚፈጸሙ ምርጫዎች እና ህዝበ ውሳኔዎችን በሙሉ እንደሚሸፍን በተብራራ ሁኔታ ገልጾታል።