Skip to main content

የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ለማስፈጸም ህዝበ ውሳኔ አስፈጻሚዎች ምልመላ

 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ለማስፈጸም ህዝበ ውሳኔ አስፈጻሚዎች ምልመላ እያከናወነ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በዚህም መሰረት ምዝገባ ሲያከናውን በቆየባቸው ቀናት የተገኘው የአመልካቾች ቁጥር መጨመር የተነሳ የህዝውሳኔ አስፈጻሚዎች ምዝገባን ዛሬ ያጠናቅቃል፡፡ በመሆኑም ለማመልከት የምትፈልጉ ዛሬ አርብ ጥቅምት 7 ቀን 2012 አ.ም እስከስራ ሰአት ማጠናቀቂያ (11 ሰአት) ድረስ ንፋስ ስልክ ቡና ቦርድ ጋር የሚገኘው የቦርዱ ማሰልጠኛ ማእከል ማመልከት የምትችሉ ሲሆን የማመልከቻው የመጨረሻ ቀን ዛሬ ነው፡፡

 

በድጋሚ የወጣ የህዝበ ውሳኔ አስፈጻሚዎች ምልመላ ማስታወቂያ

 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ህዳር 2012 ዓ.ም ለሚያካሂደው የሲዳማ የክልልነት የመደራጀት ጥያቄ ህዝበ ውሳኔ 5500 (አምስት ሺህ አምስት መቶ) የሚሆኑ የህዝበ ውሳኔ አስፈጻሚዎችን በበጎ ፍቃድ አበል ክፍያ ከአንድ ወር ላልበለጠ ጊዜ ለማሰራት ማስታወቂያ ማውጣቱ ይታወሳል ነገር ግን በቂ የሆኑ አመልካቾች ስላልተገኙ ይህንን ማስታወቂያ በድጋሚ ለማውጣት ተገዷል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከመስከረም 27- 28 ያደረገው የሁለት ቀን ዓለም አቀፍ ጉባኤ ተጠናቀቀ

መስከረም 30 ቀን 2012 ዓ.ም.

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከዩኤስኤድ እና ለዓለም አቀፍ የምርጫ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር “አገራዊ ምርጫ እና የምርጫ ባለድርሻ አካላት” በሚል ርእስ በምርጫ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያዘጋጀው የሁለት ቀን ኮንፍረንስ ተጠናቋል። በዚህ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ ከተለያዩ አገሮች የተጋበዙ እንግዶች ልምዳቸውን ያካፈሉ ሲሆን በቀጣዩ ምርጫ ሊታሰብባቸው የሚገባ ዋና ዋና አንኳር ጉዳዮችም ላይ ውይይት ተደርጓል። በክብርት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፕሬዘዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጉባኤውን የከፈቱ ሲሆን መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት አገርን በማስቀደም ለቀጣዮ ምርጫ ስኬት የበኩላቸውን አስተዋእጾ እንዲያደርጉ ጥሪ አድርገዋል። ሚዲያ፣ ሲቪል ማህበራት እና ዜጎችም ሰላምን ባስጠበቀ ግጭትን በማያስነሳ መልኩ ተሳትፎ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

Share this post

የሲቪል ማህበራት ወኪሎች የተሳትፎ ጥሪ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሲዳማ የክልልነት የመደራጀት ጥያቄ የህዝበ ውሳኔ አማራጮች አስተያየትና አመለካከቶች ከህዝብ የሚቀርብበት መድረክ ማመቻቸት ይፈልጋል፡፡ ስለሆነም በዚህ ፕሮግራም ላይ መሳተፍ የምትፈልጉ የሲቪክ ማህራትና በሲዳማ ዞን የምትንቀሳቀሱ የፓለቲካ ፓርቲዎች ይህ ማስታወቂያ ከወጣበት ቀን ጀምሮ እስከ ጥቅምት 13 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ፍላሚንጎ ፊትለፊት የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ጽህፈት ቤት ወይም በሃዋሳ ከተማ በሚገኘው የቦርዱ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ድረስ በመቅረብ እንድትመዘገቡ ቦርዱ ያሳውቃል፡፡

የሲቪል ማህበራት ወኪሎች ለምዝገባ በምትቀርቡበት ወቅት የምትሰሩበትን ዘርፍ የሚያሳይ፣ ስልጣን ከተሰጠው አካል የተሰጣችሁን የማህበራት ምዝገባ ሰነድ ይዛችሁ መቅረብ እንደሚገባችሁ በዚህ አጋጣሚ በአክብሮት ይገልጻል፡፡

የህዝበ ውሳኔ አስፈጻሚዎች ምልመላ ማስታወቂያ


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ህዳር 2012 ዓ.ም ለሚያካሂደው የሲዳማ የክልልነት የመደራጀት ጥያቄ ህዝበ ውሳኔ 6000 የሚሆኑ የህዝበ ውሳኔ አስፈጻሚዎችን በበጎ ፍቃደኝነት ለአንድ ወር ማሰራት ይፈልጋል፡፡
ስለሆነም ከታች የተዘረዘሩትን መስፈርቶች የምታሟሉ አመልካቾች የትምህርት ማስረጃችሁን ዋናውን ና ኮፒ በመያዝ ንፋስ ስልክ ቡና ቦርድ ፊትለፊት በሚገኘው የቦርዱ ማሰልጠኛ ማእከል በአካል በመገኘት ከመስከረም 24 ቀን 2012 ጀምሮ በስራ ሰአት እንድትመዘገቡ እናሳስባለን፡፡
አመልካቾች ማሟላት ያለባቸው መስፈርቶች
• የማንኛውም የፓለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆነ/ያልሆነች
• በትምህርት ዝግጅታቸው በማንኛውም የትምህርት መስክ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላት/ ያለው
• እድሜ ከ20- 45 አመት የሆነች/የሆነ
• በገጠር ቀበሌዎች ተንቀሳቅሰው መስራት የሚችሉ

የተሳሳተ ዜና ጥቆማ

መስከረም 27 ቀን 2012 ዓ.ም.

ዛሬ መስከረም 27 ቀን 2012 ዓ.ም. “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የፓለቲካ ፓርቲዎች ሊያደርጉት የነበረው ውይይት ላልተወሰነ ጊዜ ተራዘመ” በሚል ርእስ በኢትዮጵያ ብርድካስቲንግ ኮርፓሬሽን ፌስቡክ ገጽ የተዘገበው ዜና የተሳሳተ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለማሳወቅ ይወዳል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዛሬ ዕለት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ያደረገው ምንም ዓይነት ውይይትም ሆነ ድርድር ያላደረገ ሲሆን የኢቢሲም ሆነ የኢቢሲን ዜና መሠረት በማድረግ የዘገቡ ሌሎች ሚዲያዎች ዜናዎችን ከማሰራጨታቸው በፊት ማጣራት እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያሳስባል። ቦርዱ ማንኛውንም የመረጃ ጥያቄዎች ለመመለስ ዝግጁ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ ይወዳል።

Share this post

የምርጫ ክልል ሃላፊነት ስራ ምደባ ማስታወቂያ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ9ኙ ክልሎችና ለ2ቱ ከተማ አስተዳደሮች የምርጫ ክልል ሃላፊነት አወዳድሮ ለመመደብ የስራ ማስታወቂያ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ለሃረሪ ክልል፣ ለድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር፣ ለጋምቤላ ክልል፣ ለአማራ ክልል በቂ አመልካች ባለመገኘቱ ከስር የተጠቀሰውን ዝርዝር መስፈርት የምታሟሉ እና በሶስቱ ክልሎች እና በድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር መስራት ለምትፈልጉ የማመልከቻ ጊዜው ከዛሬ ከመስከረም 26 2012 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት 7 ተከታታይ ቀናት ስለተራዘመ ማመልከቻችሁን ማስገባት እንደምትችሉ ያሳውቃል፡፡

የሲዳማ ክልልነት ህዝበ ውሳኔ አፈጻጸም መርሃ ግብር ለውጥ

የሲዳማ ክልልነት ህዝበ ውሳኔ አፈጻጸም መርሃ-ግብር መሰረት የቅስቀሳ ጊዜ ከመስከረም 23 - 28 ቀን 2012 ዓ.ም በሚል ታቅዶ እንደነበረ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን የህዝበ ውሳኔ ቅስቀሳው የመራጮች ምዝገባ ከሚደረግበት ጊዜ ጋር የተቀራረበ ቢሆን ይሻላል በሚል ስለታመነበት የቅስቀሳ መርሃግብሩ ከጥቅምት 18 - 22 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ባሉት ቀናት እንዲሆን ተብሎ ተሻሽሏል፡፡ ቦርዱ በአፈጻጸም ጉዳዮች የተነሳ የሚኖሩ የቀናት ለውጥና መሸጋሸጎችን ለወደፊትም ይፋ የሚያደርግ ይሆናል፡፡


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

የተዛባ መረጃ ማስተካከያ

መስከረም 14 ቀን 2012 ዓ.ም.

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኢዜማ ፓርቲ መሪ እውነታ አዛብቶ የሚያቀርብ ንግግር ላይ ማስተካከያ የሰጠ ሲሆን ወደፊትም በተመሳሳይ ክትትል በማድረግ የተዛቡ መረጃዎችን እርምት እንደሚሰጥ ለመግለጽ ይወዳል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወሻ የኢዜማ ፓርቲ መሪ ንግግር ከስር በሚገኘው ማስፈንጠሪያ ከ4ተኛ ደቂቃ ጀምሮ ይገኛል።

Ethiopia -ESAT Bezih Samint ከፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር በወቅታዊ የሀገራችን ጉዳይ ላይ

 

Share this post