የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተለያዩ የህትመት ዉጤቶችን ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስረከበ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሕግ ከተሰጡት ኃላፊነቶች መሀከል መራጮች በቂ የምርጫ ነክ መረጃ እና ግንዛቤ የሚያገኙበትን አካታች ስልት መቀየስ እና የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም የስነ-ዜጋ እና መራጮች ትምህርትን መስጠት አንዱ ነዉ፡፡ በዚህም መሰረት የስነ-ዜጋ እና መራጮች ትምህርትን ለአካል ጉዳተኛ ማህበረሰቦች በቋሚነት ተደራሽ ለማድረግ በስፋት እየሠራ ይገኛል፡፡ይህንን ተከትሎ ግንቦት 27 ቀን 2016 ዓ.ም የተለያዩ በብሬል የተዘጋጁ የህትመት ዉጤቶችን፣ ማለትም ምርጫ በኢትዮጵያ በሚል ርዕስ የተዘጋጂ ቡክሌቶች፣ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ስነምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 አዋጆችን ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኬኔዲ እና ሕግ ላይብረሪ ክፍል አስረክቧል፡፡
በርክክብ ስነ-ስርአቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ ላይብረሪ ክፍል አባላት ይህን መሰል አካታች እና ተደራሽ የህትመት ዉጤቶች መኖራቸዉ ለአይነ-ስዉራን ተማሪዎች እና ለሌሎች የዩኒቨርሲቲዉ ማህበረሰብ አካላት ትልቅ እድል መሆኑን አንስተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድን በመወከል የተገኙት የሥነ-ዜጋ እና መራጮች ትምህርት ክፍል አባላት ቦርዱ በትኩረት እየሠራ ከሚገኝባቸዉ ተግባራት መካከል አንዱ አካታች እና ተደራሽ የሆነ የመራጮች ትምህርትን እና መረጃን ለማህበረሰቡ ማድረስ ላይ መሆኑን በመጥቀስ ይህን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታዉቋል፡፡