Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 2016 ዓ.ም. በሚያካሂደው ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫ ለሚወዳደሩ ሴት ዕጩ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት እንዲሁም ለታዛቢ ሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች እና የሰብአዊ መብት ተከታታዮች ሥልጠና ሰጠ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ6ኛው ዙር የጠቅላላ እና የድጋሚ ምርጫ ባልተካሄደባቸው የቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ የአፋር፣ የሶማሌ እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. በሚያካሂደው ምርጫ ለሚወዳደሩ ከስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ለተውጣጡ ሴት ዕጩ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ሥልጠና ሰጠ። በሥልጠናው የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉና የቦርድ አመራር አባል የሆኑት ብዙወርቅ ከተተ የተገኙ ሲሆን፤ የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ በመክፈቻ ንግግራቸው፤ ሴቶች በፖለቲካ ውስጥ በሚኖራቸው ተሣትፎ መብታቸውን ከማስከበር ባለፈ ሌሎች መብታቸው ላልተከበረ የማኅበረሰብ ክፍሎች ድምፅ በመሆን ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳላቸው ገልጸዋል። አያይዘውም ሴቶች በፖለቲካ ፓርቲ ታቅፈውም ሆነ በግል ተወዳድረው ወደ ፖለቲካ ሜዳው ሲገቡ የተሻሉና ችግር ፈቺ የሆኑ ፖሊሲዎችን በማውጣት ጉልኽ ድርሻ እንዳላቸው ጥናቶች እንደሚያመላክቱ ጠቅሰው፤ ቦርዱ ይኽን አስተዋፅዖቸውን ለማጎልበት በማሰብ የሕግ ማዕቀፎችን ከማውጣት ባለፈ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሴቶችን ወደ አመራር ለማምጣት በሚያደርጉት ጥረት ልክ የተለያዩ ማበረታቻዎችን ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።

ሜላትወርቅ ቦርዱ ሴቶችን ወደ አመራር ለማምጣት እያደረገ ያለውን ጥረት በዝርዝር ያስረዱ ሲሆን ከግንቦት 20-22 ቀን 2016 ዓ.ም. የተካሄደውን ሥልጠና ቦርዱ ሲያዘጋጅ፤ ሴት ዕጩዎቹ ተወዳድረው ወደ አመራር በመምጣት ድምፅ ለሌላት ሴትና ድምፃቸው ላልተሰማ የማኅበረሰብ ክፍሎች ድምፅ እንደሚሆኑ በማመን ጭምር እንደሆነ አስረድተዋል። በመጨረሻም ይኽን ሥልጠና ከቦርዱ ጋር በመሆን ላስተባበሩት ባለድርሻ አካላት ምስጋናቸውን ገልጸዋል።

በተያያዘ ዜና ቦርዱ ግንቦት 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ከላይ በተጠቀሱት ቦታዎች ላይ የሚያከናውነው የምርጫ ሂደት ግልፅ፣ ነፃና ገለልተኛ በሆነ መንገድ መከናወኑን ለመከታተል እና ተዓማኒነቱን ለማረጋገጥ በማሰብ፤ በምርጫ ታዛቢነት እና በሰብአዊ መብቶች ተከታታይነት ከሚሣተፉ ሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች እና ከኢትዮጰያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ለተውጣጡ ሠልጣኞች የአሠልጣኞች ሥልጠና ሰጥቷል። የሥልጠናውን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የቦርድ አመራር አባሏ ብዙወርቅ ከተተ ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም ሥልጠናው በምርጫ መታዘብ ዙሪያ ማኅበራቱ መሠረታዊ ግንዛቤ እንዲያገኙ ለማስቻል፣ የቦርዱን ዝግጅት በተመለከተ፣ ስለሥርዓተ-ፆታ እና አካታችነት፣የምርጫ ዑደት አጠቃላይ ባህሪያትን፣ የምርጫ ሪፖርትና የአዘጋገብ ቴክኒኮች የተመለከቱና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን መረዳት የበለጠ ለማጎልበት በማሰብ እንደተዘጋጀና ተሣታፊዎችም “አሣታፊ” እንዲሆን ታስቦ በተዘጋጀው ሥልጠና ላይ ሃሳባቸውን እንዲያጋሩ አበረታተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

Share this post