የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲን በተመለከተ ከቦርዱ የተሰጠ መግለጫ
የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ ሊቀመንበር ከሀገር መውጣታቸውንና ፓርቲውንም የሚመራ ሰው መወከላቸውን ከውጭ ሀገር ሆነው ለቦርዱ ሲያሳውቁ ከፓርቲው አመራሮች መኃል ይህ በሊቀመንበሩ የተሰጠው የውክልና ሥልጣን ደንቡን የተፃረረ ነው የሚል ቅሬታ ለቦርዱ አቀረቡ፡፡ ቦርዱም ሊቀመንበሩ የሰጡት የውክልና ሥልጣን ከፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንፃር የተፈፀመ መሆን አለመሆኑን መረመረ፡፡ የፓርቲው መተዳደያ ደንብ አንቀጽ 22/1/ የፓርቲው ሊቀመንበር በማይኖሩበት ወቅት ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበሩ ሊቀመንበሩን ተክተው እንደሚሰሩ ደንግጓል፡፡ በዚሁ የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ከሀገር በወጡት የፓርቲው ሊቀመንበር የተሰጠው ውክልና ደንቡን የተፃረረ በመሆኑ ቦርዱ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ በመተዳደሪያ ደንቡ አንቀጽ 22/1/ መሠረትም እንዲፈፅም ወስኗል፡፡ ይሁንና በፓርቲው አመራሮች መኃል አለመግባባቱ እየጨመረ በመሄዱ በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 74 (6) መሠረት ጉዳያቸው በባለሙያዎች ጉባኤ እንዲታይ ቦርዱ ወስኖ የባለሙያዎች ጉባኤ እያቋቋመ ይገኛል፡፡
ፓርቲው በ2015 በጀት ዓመት ከመንግሥት የሚሰጠውን ድጋፍ ከቦርዱ ብር 1,184,259.85 (አንድ ሚሊዮን አንድ መቶ ሰማንያ አራት ሺህ ሁለት መቶ ሃምሣ ዘጠኝ ብር ከሰማንያ አምስት ሣንቲም) ወስዷል፡፡ በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 82/2/ መሠረት ፓርቲዎች ስለወሰዱት የመንግሥት ድጋፍ የኦዲት ሪፖርት የማቅረብ ግዴታ አለባቸው፡፡ ይሁንና የኦዲት ሪፖርቱን ፓርቲው ሳያቀርብ በመቅረቱ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንዲያቀርብ ሳያቀርብ ቢቀር ፓርቲው የመሰረዝ ዕጣ ፈንታ እንደሚገጥመው በማሳሰብ ቦርዱ ለፓርቲው አሳውቋል፡፡ ይሁንና ፓርቲው ይህንንም ሪፖርት እስከ ዛሬው ቀን ድረስ አላቀረበም፡፡
በአመራሮቹ መኃል ያለውን ልዩነት በፓርቲው ደንብና በአዋጅ 1162/2011 መሠረት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ባለበት ሁኔታ፤ እንዲሁም ከግብር ከፋዮች ተሰብስቦ ለፓርቲው የተሰጠውን የድጋፍ ገንዘብ እንዲያወራርድ በሕጉ መሠረት ፓርቲው ተጠይቆ እያለ፤ በተለያዩ ማኅበራዊና መደበኛ ሚዲያዎች ላይ በመቅረብ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት የቦርዱን ጥረት እያንኳሰሱ ሥሙንም የማጥፋት ሥራ ጥቂት የፓርቲው አመራሮች እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም ቦርዱ ይህን መግለጫ ለመስጠት ተገዷል፡፡
እንደሚታወቀው ቅሬታ አለኝ የሚል ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራርም ሆነ የፖለቲካ ፓርቲ አባል በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብና በምርጫ አዋጁ የተቀመጡ የቅሬታ አቀራረብ ሂደቶችን ተከትሎ ቅሬታውን ማቅረብ እንዲሁም ቦርዱም በሚሰጠው ውሣኔ ቅር የተሰኘ አካልም ጉዳዩን ለፍርድ ቤት ማቅረብ እንደሚችል በአዋጁ በግልፅ ተደንግጓል፡፡ በዚሁ መሠረትም ጉዳያቸውን ለከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበው እየታየ ይገኛል፡፡
ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ እያለ ቦርዱም ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ባለበት ሁኔታ የቦርዱን ስም በማይገባ እና በተሳሳተ መንገድ የተለያዩ ሚዲያዎችን በመጠቀም የሚካሄድን የስም ማጥፋት ተግባር ቦርዱ እንደማይቀበለው አጥብቆ እየገለፀ ይህ የስም ማጥፋት እና የተሳሳተ መረጃ የማሰራጨት ሂደት በፓርቲው ጥቂት አመራሮች የሚቀጥል ሆኖ ቢገኝ ቦርዱ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ የሚገደድ መሆኑን አጥብቆ ያሳስባል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ሚያዝያ 24 ቀን 2ዐ16 ዓ.ም.