የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) በጎዴ ከተማ ከጥቅምት 22 ቀን 2012 ዓ.ም እስከ ህዳር 2 ቀን 2012 ዓ.ም 4ኛ ብሔራዊ ኮንግረሱን በማከናወን የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ እና መመስረቻ ጽሁፍ ማሻሻሉን፤የአመራር ምርጫ ማካሄዱን ለቦርዱ መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም በአስገባው ሰነዶች አማካኝነት አሳውቋል፡፡

ይሁንና ሰነዶቹ በሚመለከተው የቦርዱ የሥራ ክፍል በወቅቱ ተመርምረው ለሥራ አመራር ቦርዱ ከውሳኔ ሃሳብ ጋር ሳይቀርቡ ቀርተዋል፡፡ እንዲያውም የጉባኤው ሰነዶች ጠፍተው ከብዙ ፍለጋ በኋላ ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም ነው የተገኙት፡፡ ይህ በጊዜው በነበረው የቦርዱ የአሰራር ክፍተት የተፈጠረን ሁኔታ ፓርቲው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ መፍጠር ስለማይኖርበት ጥፋቱን የፈጸሙት የቦርዱ የሥራ ክፍል ሰራተኞች ላይ የእርምት እርምጃ በመውሰድና ከፓርቲው ሕልውና አንፃር ጉዳዩን እንደገና መመርመር ተገቢ መሆኑን ቦርዱ ተገንዝቧል፡፡

በዚሁ መሰረት የአሠራር ክፍተቱን በፈጠሩት ሠራተኞች ላይ እርምጃ ተወስዷል፡፡ እንዲሁም የጎዴውን ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔዎች እውቅና አለመስጠት ፓርቲው በጎዴው ጉባኤ ውሳኔ መሰረት ለአራት ዓመታት ያከናወናቸውን ተግባራት ዋጋ አልባ ማድረግ መሆኑ ታምኗል ፡፡

በመሆኑም የፓርቲውን ሕልውና በቦርዱ የተፈጠረው የአሠራር ክፍተት ሊፈታተነው አይገባም በማለት ቦርዱ የጎዴው ጉባኤ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎችም ሆኑ የውሳኔዎቹን ውጤቶች ተቀባይነት ሊኖራቸው እንደሚገባና እንዲሁም ፓርቲው ቀጣዩን ጠቅላላ ጉባኤ ይህ ውሳኔ ከደረሰው ቀን ጀምሮ ባሉት 3 ወራት ውስጥ እንዲያደርግ ሲል ጥቅምት 2 ቀን 2016 ዓ.ም በአካሄደው ስብሰባ ወስኗል፡፡

ጥቅምት 27 ቀን 2016 ዓ.ም.

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ