የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልል በሚገኙ ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች ማለትም በጋሞ፣ ጎፋ፣ ወላይታ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ጌዲዮ እና ኮንሶ ዞኖች እንዲሁም ቡርጂ፣ ደራሼ፣ ባስኬቶ፣ አሌ እና አማሮ ልዩ ወረዳዎች ላይ የሚካሄደውን ሕዝበ ውሣኔ በተመለከተ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሆነ ይታወቃል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የምርጫ ቦርዱ በሕዝብ ውሣኔው ላይ በሚነሡ የተለያዩ ሃሳቦች ላይ የሚደረገውን ክርክር ለማስተባበር ይፈልጋል። በመሆኑም ቦርዱ በዚሁ ጉዳይ ላይ ፍላጎት ያላችሁ ተቋማት እና መገናኛ ብዙኃንን በተናጠል ወይም በጋራ በመሆን ክርክር የማዘጋጀት ዝርዝር የፍላጎት መግለጫ (Expression of interest) እንድታቀርቡ ጥሪ ያቀርባል።
ማንኛውም በህዝበ ውሳኔ ዙርያ ክርክር ወይም ውይይት ለማዘጋጀት የሚያስብ ተቋም የሚመለከቱትን ዋና ዋና ነገሮችን የያዘ የፍላጎት መግለጫ ሰነድ ሊያቀርብ ይገባል።
• የክርክሩን ወይም የውይይቱን ርእስ እና አላማ የሚገልፅ አጭር ፅሁፍ (concept note) ክርክሩ ወይም ውይይቱ የሚከናወንበት መንገድ (mode of engagement)
• ክርክሩ ወይም ውይይቱ የሚመራበት ስርዐት (code of conduct)፤
• የተሣታፊዎች አጠቃላይ ዝርዝር እና ብዛት፤
• ክርክሩ ወይም ውይይቱ ለሕዝብ የሚቀርብበት ሁኔታ፤
• የአከራካሪ አመራረጥ ሂደት፣ መሥፈርት እና መመዘኛ
• ክርክሩ ለሕዝብ የሚቀርብበት መንገድ
• በጀት እና የገንዘብ ምንጭ እና
• ክርክሩ የሚከናወንባቸው ቋንቋዎች።
የፍላጎት መግለጫ ወረቀቱ እስከ ይህ ማስታወቂያ ከወጣበት ጥቅምት 28 ጀምሮ በmedia [at] nebe.org.et የኢ-ሜል አድራሻ በመላክ ወይም በቦርዱ ዋና መሥሪያ ቤት 3ኛ ፎቅ ቢሮ ቁ 301 በግንባር በመገኘት አስከ ህዳር 9 ቀን 2015 ዓም ድረስ ማስገባት ይችላል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ