የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአካባቢ ምርጫ የሕግ ማዕቀፍ እና አፈጻጸምን የተመለከተ ያስጠናው ጥናት ላይ ባለድርሻ አካላትን አወያየ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነሐሴ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. የአካባቢ ምርጫ የሕግ ማዕቀፍ እና አፈጻጸምን የተመለከተ ያስጠናው ጥናት ላይ ባለድርሻ አካላትን አወያየ። የውይይቱ ዋና ዐላማ በኢትዮጵያ ለ5ኛው ጊዜ የሚካሄደውን የአካባቢ ምርጫ ለማከናወን በሚደረገው ዝግጅት ላይ የአካባቢ ምርጫን አጠቃላይ ባህሪና አሠራር አስመልክቶ ምርጫ ቦርዱ ባስጠናው ጥናት ላይ ጥናቱ የተከናወነባቸውን ሳይንሳዊ ዘዴዎች፣ በጥናቱ የተገኙ ልምዶችን ፣ ተግዳሮቶችን፣ እንዲሁም ምክረ ሃሳቦችን ጥናቱን ባካሄዱት በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የፈደራሊዝም እና አስተዳድር ጥናት/ ትምህርት ክፍል (Centre for Federalism and Governance Studies Addis Ababa University) በሚሠሩ ከፍተኛ የዘርፉ ተመራማሪዎች በማቅረብ አፈጻጸሙን አስመልክቶ ባለድርሻ አካላትን በማወያየት ሃሳብ ለመሰብሰብ ያለመ ነው።
በውይይቱ ላይ የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳን ጨምሮ ሁሉም የቦርድ አመራር አባላትና የቦርዱ የማዕከልና የክልል መሥሪያ ቤት ባልደረቦች የተገኙ ሲሆን፤ ከባለድርሻ አካላትም እንዲሁ ከፖለቲካ ፓርቲ፣ ከሲቪል ማኅበራት፣ ከተወካዮች ምክር ቤት፣ ከፌደራልና ከክልል መንግሥታት፣ እንዲሁም ከፀጥታ አካላትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ተወካዮች ተገኝተውበታል።
ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም በዚህ በአስፈላጊነቱ እጅግ ጉልህ በሆነው የአካባቢ ምርጫን አስመልክቶ በተደረገ ጥናት ላይ ሃሳብና አስተያየታቸውን ለመስጠት ለተገኙት ባለድርሻ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የአካባቢ ምርጫን ማስፈፀም እንደየአካባቢው የራሱ ተግዳሮት እንደሚኖረው የገለጹት ሰብሳቢዋ ስኬቱን ለማረጋገጥ ጥናቶችን ማሰጠናቱ አስፈላጊ እንደሆነ በቦርዱ ታምኖበት ከባለሞያዎች ጋር በመነጋገር እንደተከናወነ አስረድተዋል። በጥናቱም ዓለም ዐቀፍ ተሞክሮዎችንና እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አዳጊ ሀገራትን ተሞክሮዎች ለማካተት እንደተሞከረና የአካባቢ አስተዳደር ሊኖረው የሚገባውን ቅርፅና ማዕቀፍ እንዲሁም የሥልጣን ወሠን ባካተተ መልኩ እንደተከናወነ ገልጸዋል። የአካባቢ ምርጫን አስፈላጊነት በገለጹበት ንግግራቸውም በወካዩንና ተወካዩ መኻል የሚኖረውን ርቀት የሚያጠብና ሥልጣንን ለዜጎች ለመቆጣጠር መሠረት እንደሆነ አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።
ጥናቱን ዘመላክ አየለ (ፒ.ኤች.ዲ) እና ክርስቶፍ ቫንደር (ፒ.ኤች.ዲ) ለተሣታፊዎች ያቀረቡት ሲሆን፤ የጥናቱ ጭብጥ ዓለም ዐቀፍ የአካባቢ ምርጫ ሕጎችን እና ተሞክሮዎችን ገምግሞ፣ ቦርዱ ከዚህ በኋላ ለሚያከናወነው የአካባቢ ምርጫ እንደ’መመሪያ ሊያገለግሉ የሚችሉ የማሻሻያ ሃሳቦችን ማዘጋጀት/ማቅረብ ሲሆን ከዚህ በፊት የተካሄዱ የአካባቢ ምርጫዎችን ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች በመለየት ለቀጣይ የአካባቢ ምርጫ ጠቃሚ ሠነድ ማዘጋጀት፣ የየክልሎችን የአካባቢ ምርጫ የምክር ቤት ቁጥር ለመወሰሠ የወጡ ዐዋጆች እና የዐዋጅ ማሻሻያዎችን መመርመር ከዐዋጆቹ በመነሣት ማሻሻያ ሀሳቦችን ማቅረብን እንደ ዝርዝር ዐላማ ይዞ የተነሣ ነው።
በባለሞያዎቹ የቀረበውን የመጀመሪያ ደረጃ የጥናት ውጤት ተከትሎ ጥናቱን ይበልጥ ለማዳበር የሚያስችለውን ሃሳብና አስተያየት ከባላድርሻ አካላቱ የተሰበሰበ ሲሆን፤ ባለድርሻ አካላቱም ቦርዱ ይህን ጥናት አስጠንቶ የባለድርሻ አካላቱን አስተያየት ለመሰብሰብ መድረኩን ማዘጋጀቱን አድንቀው፤ በማስከተልም አስተያየታቸውን አጋርተዋል። ከተሰጡ አስተያየቶች ውስጥም ቀደም ሲል ሀገራዊ ምርጫውን ለማካሄድ ጥቅም ላይ የዋለው ሕግ ለአካባቢ ምርጫው የሚኖረው ፋይዳ፣ የአካባቢ ተመራጮች ከክልልና ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚኖራቸው በጀትን የተመለከተ ግንኙነት፣ ማኅበረሰቡና ባለድርሻ አካላቱ ስለአካባቢ ምርጫ ሊኖራቸው የሚገባው ግንዛቤና ይህንኑ ግንዛቤ ለማስጨበጥ መከተል ስለሚገባው አማራጮች በባለድርሻ አካላቱ ከተነሰት አስተያየቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ።
በተሣታፊዎቹ ለተነሡት አስተያየቶች ባለሞያዎቹ መልስ የሰጡበት ሲሆን፤ በምርጫ ቦርዱ ከፍተኛ ቁጥጥር የሚደረግበት በክልል መንግሥታት ደረጃ የሚዘጋጅ የቀበሌ ምርጫ አስተዳደር፤ በግልጽ ገደብ የተበጀለት ኃላፊነት ለክልልና ለአካባቢ የምርጫ ቢሮዎች መስጠትና የነዚህን ቢሮዎችን ሥልጣንና ኃላፊነት በዝርዝር የያዘው መመሪያው አካባቢዎቹ የሚኖራቸውን የመፈጸም ነፃነትና ለበላይ አካል የሚኖራቸውን ተጠያቂነት በበቂ ማቻቻል የሚያስገኝ ሆኖ መዘጋጀት እንዳለበት ምክር ሃሳብ አቅርበዋል። የቦርዱ ዋና ሰብሳቢም የተሰሡ አስተያየቶችን ባካተተ መልኩ ቦርዱ አዳብሮት ውሣኔ እንደሚሰጥበትና ዝርዝር አፈጻጸሙም ይህን ተከትሎ እንደሚሆን አሳውቀዋል።