Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሥነ ዜጋ ትምህርት ቀጣይነት ዙሪያ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አካሔደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሥነ ዜጋ ትምህርት ቀጣይነት ዙሪያ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ባለድርሻ አካላት ጋር ግንቦት 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ምክክር አካሄደ፡፡ በቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ ንግግር የተከፈተው የምክክር መድረኩ፤ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ተቋማት የሥነ ዜጋና የመራጮች ትምህርት ተሣትፎ ምርጫ በሚደረግባቸው ዓመታት ላይ ብቻ ተወሥኖ እንዳይቀር ግንዛቤ እንዲወሰዱ ለማድረግና በሥነ ዜጋ ትምህርት ቀጣይነት ላይ የቦርዱ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሚና ላይ ግንዛቤ መፍጠር ዐላማው ያደረገ ሲሆን፤ መድረኩ ላይ ከቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ በተጨማሪ የቦርድ አመራር አባል የሆኑት አበራ ደገፋን (ዶ/ር) ጨምሮ የቦርዱ የጽ/ቤት ኃላፊዋ ሜላትወርቅ ኃይሉ ተገኝተውበታል። ከባለድርሻ አካላትም ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በተጨማሪ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተወካዮችና የዘርፉ ባለሞያዎች፤ እንዲሁም የብዙኃን መገናኛ አካላት በተገኙበት ተካሂዷል።

ምክትል ሰብሳቢው በመክፈቻ ንግግራቸው በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ዜጎች በመምረጥ ተሣትፈው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ቦርዱ ባደረጋቸው ጥረቶች ላይ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና የመገናኛ ብዙኃኑ አስተዋጽዖ ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰው፤ ይህ አስተዋጽዖ በምርጫ ወቅት ብቻ ሳይወሠን ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባ አሳስበዋል። በተለይም የትምህርት ተቋማት በመራጮች እና በሥነ ዜጋ ትምህርት አሰጣጥ የቦርዱ አንደኛው አጋር መሆናቸው በዐዋጅ መደንገጉን ጠቅሰው፤ የትምህርት ዘርፍ ዋነኛ ባለቤት የሆኑት ትምህርት ተቋማቱ በቀጣይ ከቦርዱ ጋር አብረው የሚሠሩበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹም ጠይቀዋል።

ምክትል ሰብሳቢውን ተከትሎ የተናገሩት የቦርድ አመራር የሆኑት አበራ ደገፋ (ዶ/ር) የመራጮች ትምህርት በምርጫ ወቅት ብቻ ሊወሠን እንደማይገባ በድጋሚ አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል። በመድረኩ ላይ የሕግ ባለሞያው ደበበ ኃይለገብርኤል በሥነ ዜጋ እና የመራጮች ትምህርት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ሚና በተመለከተ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በቦርዱ የሥነ ዜጋና መራጮች ትምህርት ክፍል አማካኝነት በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ተቋማት የሥነ ዜጋ እና መራጮች ትምህርት ተሣትፎ ምን ይመስል እንደነበር ገለጻ የተደረገ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የሥነ ዜጋ ትምህርትን ቀጣይነት ለማረጋገጥ በአፈጻጸም ደረጃ ከማን ምን ይጠበቃል በሚለው ላይ ደግሞ ሽመልስ ሲሳይ (ዶ/ር) ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የሥነ ዜጋና የመራጮች ትምህርት መለኪያውን ምርጫ ቦርድ ቢያወጣውም የዲሞክራሲ ተቋማት ትልቅ አስተዋጽዖ እንደሚኖራቸው፤ በደንብ የተደራጁ ሲሆኑ ደግሞ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ታች ወርዶ ማኅበረቡን በማወቅና በማንቀሳቀስ ረገድ ትልቅ ዐቅም አላቸው ብለዋል። ብዙኃን መገናኛ አካላቱም ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ከቻሉ በአንድ ጊዜ ብዙ አካላትን በመድረስ ሥነ ዜጋን በማስተማር የሚኖራቸውን ትልቅ አበርክቶንም እንዲሁ አስረድተዋል። የዓለም ዐቀፍ ተሞክሮዎችንም ሲያብራሩም መገናኛ ብዙኃኑ ላይ የሥነ ዜጋ ትምህርት ለሚሠሩ አካላት የዓየር ሰዓት መስጠት በሕግ ግዴታ የሚጥሉ ሀገራት እንዳሉ ጠቅሰው፤ ፓለቲከኞችም የተለያዩ አጀንዳዎቻቸው እንዳሉ ሆነው ዜጎች መሠረታዊ መብቶቻቸውን እንዲያውቁ ከማድረግ አንጻር ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም በካሪኩለሙ ላይ ከተቀመጠው አልፈው በስፋት ሊሠሩበት እንደሚገባ አብራርተዋል።

በተጨማሪም ባለሞያዎቹ፤ ባለድርሻ አካላቱ እነማን ናቸው የሚለው በደንብ ተለይቶ ዕቅድ በማውጣት ትምህርቱን ምርጫ ከመድርሱ በፊት ገንዘብና ጊዜን ባገናዘበ ሁኔታ በምን ያህል ጊዜ ምን ያህል ዜጎችን መድረስ እንችላለን የሚለውን በመለየት መሥራት እነደሚገባ ያስረዱ ሲሆን፤ በየጊዜውም የክትትልና ግምገማ ሥርዓት በማበጀት ውጤቱን መመዘን እንደሚገባ አሳስበዋል።

የመድረኩ ተሣታፊዎች በበኩላቸው ቦርዱ በምርጫ ወቅት ሳይወሠን የሥነ ዜጋ እና የመራጮችን ትምህርትን የተመለከተ መድረክ ማዘጋጀቱን በበጎ በማንሣት፤ በቀጣይ ቢስተካከሉ ያሏቸውን ጉዳዮች እንዲሁም ቦርዱና መንግሥት ቢያደርጓቸው ያሏቸውን ድጋፎች ዘርዝረዋል፡፡ የሥነ ዜጋ ትምህርት፤ በተለይም ለመራጮች ትምህርት የሚሰጠው ጊዜ በጣም ያነሰ እንደሆነና እንዲጨመር፣ ለዘርፉ የሚሰጠው የፋይናንስ ድጋፉም በቂ ባለመሆኑ ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሆነባቸው፣ በመንግሥትም የሚሰጣቸው ትኩረት የሚያበረታታ መሆን እንደሚገባውና የሥነ ዜጋ ትምህርት ተቋማዊ ሆኖ ባልተቋረጠ ሁኔታ መሰጠት እንዳለበት ከተሣታፊዎች ከተሰጡ አስተያየቶች ይጠቀሳሉ።

ለተሣታፊዎች አስተያየት ምላሽ የሰጡት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አመራሮች፤ ቦርዱ ዐቅሙ በፈቀደው መጠን ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመው፤ ለሚፈለገው መሻሻልና ለውጥ ተቋማቱ የሚያደርጉት ጥረት ወሣኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻም የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡

Share this post