የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ-ምግባር ዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 100 ንዑስ አንቀጽ ሁለት በተሰጠው ሥልጣን መሠረት መንግሥት ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ ለመወሠን መመሪያ አጽድቆ በሥራ ላይ በማዋል በ2013 በጀት ዓመት በመመሪያው መሠረት በማከፋፈል የፓርቲዎቹን ድርሻ ፓርቲዎቹ በከፈቱት የተለየ የባንክ ሒሣብ ቁጥር ገቢ ማድረጉ ይታወቃል፡፡

በዚሁ መሠረት ፓርቲዎቹ በባንክ ሒሣብ ቁጥራቸው ገቢ የሆነውን የፋይናንስ ድጋፍ በመመሪያው አንቀጽ 10 መሠረት በአግባቡና ለታለመለት ተግባር ብቻ የፋይናንስ ሕጉን በመከተል በሥራ ላይ በማዋል የበጀት ዓመቱ በተጠናቀቀ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ በተመሰከረለት የውጭ ኦዲተር በማስመርመር በወቅቱ ለቦርዱ ሪፖርት እንዲያቀርቡ ተደንግጓል፡፡

ይሁንና የተለያዩ ፓርቲዎች በ2013 በጀት ዓመት በመሥፈርቱ መሠረት ተከፋፍሎ በፓርቲው የተለየ የባንክ ሒሣብ ቁጥር ገቢ የተደረገውን የፋይናንስ ድጋፍ አስመልክቶ በሕጉ መሠረት የኦዲት ሪፖርት እና የገንዘብ መቀበያ ደረሰኝ ማቅረብ ቢኖርባቸውም ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ፓርቲዎች ግን የኦዲት ሪፖርቱን በተሟላ መልኩ ያላቀረቡ መሆናቸው ታውቋል፡-

ሀ/ የገንዘብ መቀበያ ደረሰኝ አቅርበው የኦዲት ሪፖርታቸውን ያላቀረቡ

 1. የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ)
 2. የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)
 3. የራያ ራዩማ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ራዴፓ)
 4. የጋምቤላ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ጋሕነን)
 5. የአፋር ሕዝብ ፓርቲ (አሕፓ)
 6. የአፋር ነፃ አውጭ ግንባር ፓርቲ (አነግፓ)
 7. ኅዳሴ ፓርቲ (ኅዳሴ)

ለ/ የኦዲት ሪፖርት እና የገንዘብ መቀበያ ደረሰኝ ያላቀረበ

 1. የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)
 2. የኦሮሞ ነፃነት ንቅናቄ (ኦነን)
 3. ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኅብር ኢትዮጵያ)
 4. የምዕራብ ሶማሌ ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ምሶዲፓ)
 5. የጌዴኦ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ጌሕዴድ)
 6. የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር (አርዱፍ)
 7. ዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ለሉዓላዊነት (ዓረና)
 8. የሐረሪ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ሐዲድ)
 9. ሞቻ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሞዴፓ)
 10. የካፋ አረንጓዴ ፓርቲ (ካአፓ)
 11. የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ጋዴፓ)
 12. የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ዎብን)
 13. የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ)
 14. የአገው ብሔራዊ ሸንጎ (ሸንጎ)
 15. የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ)
 16. ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ

ሐ/ የኦዲት ሪፖርት አቅርቦ የገንዘብ መቀበያ ደረሰኝ ያላቀረበ

1. የጋምቤላ ሕዝብ ነፃነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋሕነዴን)

በመሆኑም የተያዘው የ2014 በጀት ዓመት ሊጠናቀቅ ሁለት ወራት የማይሞላ ጊዜ ስለቀረው፤ ለበጀት ዓመቱ የተመደበው ድጋፍ በባንክ ሒሣብ ቁጥር ገቢ እንዲደረግ ያለፈው የ2013 በጀት ዓመት ድጋፍ የኦዲት ሪፖርትና ገንዘቡ ለፓርቲዎቹ ገቢ የተደረገበትን የገንዘብ መቀበያ ደረሰኝ በአስቸኳይ እንዲያቀርቡ ቦርዱ ያሳውቃል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ማስታወቂያ
ግንቦት 09 ቀን 2014 ዓ.ም.