በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና በኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መካከል ከቁጫ ምርጫ ክልል ድምጽ መስጫ ወረቀት ጋር በተያያዘ በጠቅላይ ፍ/ቤት በሰበር ሰሚ ችሎት በመቁ. 211141 ሲካሄድ በነበረው ክርክር ነሐሴ 21 ቀን 2013 ዓ.ም በዋለው ችሎት ድጋሚ ምርጫ እንዲደረግ ውሳኔ መስጠቱ ይታወሳል።
ከውሳኔው በኋላ በፓርቲው በኩል በተደረጉ ለውጦች የተነሳ ማለትም የፓርቲው ሁለት እጩዎች ከምርጫ ውድድሩ ራሳቸውን በፈቃዳቸው ማግለላቸውን በ10/01/2014 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ ለቦርዱ በማሳወቃቸው፣ እንዲሁም ሌላዋ የፓርቲው ዕጩ ተወዳዳሪ ፓርቲውን ወክለው እንዳይወዳደሩ የፓርቲው የወረዳ ጽ/ቤት ያገዳቸው መሆኑን በ28/01/2014 ዓ.ም በማሳወቁ፣ ፓርቲውም በዚህ ምርጫ ክልል ስላሉት እጩዎች ማብራሪያ ሲጠየቅ ራሳቸውን ማግለል አይችሉም የሚል ምላሽ ከመስጠት ውጪ ተጨማሪ ሃሳብ ባለማቅረቡ ቦርዱ የውሳኔውን አፈጻጸም አስመልክቶ ውሳኔ የሰጠውን ፍርድ ቤት ማብራሪያ ጠይቋል።
ፍ/ቤቱ ስለአፈጻጸሙ ማብራሪያ ሲጠየቅ ከፍርዱ በኋላ አዲስ ሁኔታ ከተፈጠረ በዚያው መሠረት ቦርዱ መወሰን ይችላል የሚል ትዕዛዝ በመስጠቱ ይህንኑ መሠረት በማድረግ ፓርቲው ሁለቱም በገዛ ፈቃዳቸው ላለመወዳደር የወሰኑትን ዕጩዎች የሚተኩ ዕጩዎች በወቅቱ ባለማቅረቡ እንዲሁም አንደኛዋ ዕጩ በፓርቲው የወረዳው ጽ/ቤት ከውድድሩ እንዲወጡ በመወሰኑ እንደፍርዱ ድጋሚ ምርጫ ለማድረግ መሠረት የሆነው የውሳኔው ሁኔታ የተቀየረ በመሆኑ ደግሞ ምርጫ ለማድረግ የማይቻለው መሆኑን ቦርዱ ተገንዝቧል፡፡
በመሆኑም በቁጫ ምርጫ ክልል ድጋሚ ምርጫ ይደረግባቸው በማለት ፍ/ቤቱ በሰጠው ውሳኔ እና ትዕዛዝ መሠረት ዳግም ምርጫውን ማከናወን የማይቻለው መሆኑን ቦርዱ ጥቅምት 26 ቀን 2014 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የወሰነ መሆኑን ቦርዱ እያሳወቀ በምርጫ ክልሉ የሚገኘው ሕዝብም ያለ ተወካይ እንዳይቀር ለክልል በምክር ቤቱ አሸናፊ ናቸው ተብለው በቦርዱ የተወሰኑት ዕጩ ተወዳዳሪዎች በምክር ቤቱ ተገኝተው የክልላቸው ሕዝብ ሕጋዊ ወኪል ሆነው እንዲያገለግሉ መወሰኑን ቦርዱ ለማሳወቅ ይወዳል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ህዳር 07 ቀን 2014 ዓ.ም