የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ተኛው ጠቅላላ ምርጫ ተግባራትን እያከናወነ እንደሆነ ይታወቃል፣ በዚህም መሰረት የተወሰኑ ተቋማት በተወዳዳሪዎች መካከል የምርጫ ክርክር ለማከናወን ከቦርዱ ፍቃድና አቅጣጫ ለማግኘት ጥያቄዎችን አቅርበዋል።

ይህንን እንዲሁም ሌሎች ልምዶችን መሰረት በማድረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የእጩዎች ምዝገባ ተጠናቆ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ከታወቁ በኋላ አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክርን ለማስተባበር ይፈልጋል። በመሆኑም ከዚህ በፊት ጥያቄ/ ማብራሪያ ያስገባችሁም ሆነ በዚሁ ጉዳይ ላይ ፍላጎት ያላችሁ መንግስታዊ ያልሆናችሁ ተቋማት እና ሚዲያዎች በተናጠል ወይም በጋራ የምርጫ ክርክር ዝርዝር የፍላጎት መግለጫ ወረቀት (Expression of interest) ለቦርዱ እንድታቀርቡ ጥሪ ያቀርባል።

የፍላጎት መግለጫ ማካተት የሚገባቸው ዋና ዋና ሃሳቦች

ማንኛውም የምርጫ ክርክር ለማከናወን የሚያስብ ተቋም የሚመለከቱትን ዋና ዋና ነገሮችን ያሟላ የፍላጎት መግለጫ ሊያቀርብ ይገባል።

- ሊያከናውኑት ያቀዱት ክርክር ግልጽ አላማ
- ሊያከናውኑት ያቀዱት ክርክሩ የሚከናወንበት መንገድ (mode of engagement)
- ሊያከናውኑት ያቀዱት የክርክሩ ስነምግባር ደንብ (code of conduct)
- የክርክሩ ቁጥር ብዛት፣ የተሳታፊዎች ሁኔታ፣ ለህዝብ የሚቀርብበት ሁኔታ
- የአከራካሪ አመራረጥ ሂደት፣ መስፈርት እና መመዘኛ
- ክርክሩ ለህዝብ የሚቀርብበት መንገድ
- በጀት እና የገንዘብ ምንጭ
- ክርክሩን የሚከናወንባቸው ቋንቋዎች እና የመሳሰሉት

ከላይ ከተጠቀሱት ዋና ዋና ጉዳዮች በተጨማሪ ምክረሃሳብ የሚያስገቡ ተቋማት አስፈላጊ ነው የሚሉትን ዝርዝር እቅድ በምክረሃሳባቸው ውስጥ አካተው ማቅረብ ይችላሉ። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ክርክሩን በማመቻቸት ብሔራዊ ክርክር መከናወንን ከማመቻቸት በተጨማሪ ለክርክር ዝግጅት የሚሆን የፋይናንስ ድጋፍ አያደርግም።

የፍላጎት መግለጫ ወረቀት እስከ የካቲት 26 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ (በአምስት የስራ ቀናት ውስጥ) በቦርዱ ዋና መስሪያ ቤት በግንባር ወይም በ media [at] nebe.org.et ኢሜይል አድራሻ ሊቀርብ ይችላል።

የጥሪ ማስታወቂያ
የካቲት 18 ቀን 2013 ዓ.ም