የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ 673 የምርጫ ክልሎችን በመክፈት የእጩዎች ምዝገባን እያከናወነ እንደሆነ ይታወሳል።
ቦርዱ የእጩዎች ምዝገባን ለመጀመር የምርጫ ክልል ቢሮዎችን ዝግጅት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተለያዩ ትብብሮችን ከክልል መንግስታት እና ከከተማ መስተዳድሮች ሲጠይቅ እንደነበር በአንዳንድ ክልሎች በትብብሮቹ መዘግየትም የተነሳ የእጩዎች ምዝገባ በሁለት ዙር እንዲያደርግ መገደዱ ይታወሳል። ከዚያም በተጨማሪ የትራንስፓርት ትብብሮች አስቸጋሪ ከመሆናቸው የተነሳ የተለያዩ የምርጫ ክልል ቢሮዎች መከፈትም ዘግይቶ የእጪዎች ምዝገባ ሊራዘም ችሏል።
የምርጫ ክልሎች ከተከፈቱም በኋላ ደህንነታቸውን የማስጠበቅ ሃላፊነት የክልል እና የከተማ መስተዳድሮች ነው። ቦርዱ በተለያየ ጊዜ የምርጫውን ደህንነት ለማስጠበቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይቶች እና ንግግሮቸን እያደረገ የቆየ ሲሆን በዚህም መሰረት አብዛኛው የምርጫ ክልሎች ጥበቃ ሊሟላላቸው ችሏል። ለዚህም ቦርዱ ከፍተኛ ምስጋናውን ያቀርባል።
ይህንንም ነገር ግን አሁንም ቢሆን
• በኦሮሚያ ክልል- 21 የምርጫ ክልሎች
• በሶማሌ ክልል- 31 የምርጫ ክልሎች
• አማራ ክልል- 40 የምርጫ ክልሎች
• በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል- 6 የምርጫ ክልሎች ጥበቃ አልተመደበላቸውም። በመሆኑም አስፈላጊውን የደህንነት ከለላ ከክልል መንግስታቱ እያገኙ አይደለም።
ስለዚህ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ክልሎች በአስቸኳይ ለቀሪ የምርጫ ክልል ቢሮዎች የጥበቃ ምደባ እንዲያከናውኑ ነገር ግን ይህ ሳይሆን ቀርቶ በጥበቃ ችግር ሊፈጠሩ የሚችሉ የምርጫ አፈጻጸም ችግሮች ክልል መስተዳድሮች እና የጸጥታ አካላት ሃላፊነቱን እንደሚወስዱ ያስገነዝባል።