የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ የተለያዩ ዝግጅቶቸን ሲያከናውን መቆየቱ ይታወሳል። ግንቦት 7 ቀን 2013 ቦርዱ ከፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረገው ምክክር የድምፅ መስጫ ቀን በታቀደለት ግንቦት 28 እና ሰኔ 05 ቀን 2013 መከናወን እንደማይችል በተጨማሪ ከ2-3 ሳምንት ዝግጅት ጊዜ እንደሚያስፈልግ ገልጿል።

በዚህም መሰረት የሚከተሉት ዋና ዋና ተግባራት በተጨማሪዎቹ ቀናት የሚከናወኑ ይሆናል።

1. ተጨማሪ የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላን ማጠናቀቅ

በአሁኑ ወቅት ከሚገኙት 138,655 የምርጫ አስፈጻሚዎች በተጨማሪ ቦርዱ 106,345 ምርጫ አስፈጻሚዎችን መልምሎ ማሰልጠን ይኖርበታል፣ ከነዚህ መካከል በቦርዱ መጠባበቂያ ዝርዝር ላይ ተጨማሪ 100,333 አስፈጻሚዎች አሉ። ከእነዚህ ተጨማሪ ምርጫ አስፈጻሚዎች በቦርዱ በተጠባባቂነት የተያዙ ሲሆን ቦርዱ መስፈርቱን የማጣራት እና የማሰልጠን ስራ አጠናቆ ለድምጽ መስጫ ቀን ዝግጁ ያደርጋል። ከፍተኛ የአስፈጻሚ ቁጥር ክፍተት ባለባቸው ክልሎች በልዩ ሁኔታ ለመሙላት ጥረት ያደርጋል።

2. ስልጠና

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለድምጽ መስጫ ቀን ሁሉንም የምርጫ አስፈጻሚዎች ያሰለጥናል። ይህ ስልጠናም

  1. የመሪ አሰልጣኞች ስልጠና - 20 ሰዎች በማእከል ደረጃ
  2. በዋና አሰልጣኞች ስልጠና- 220 ሰዎች በማእከል ደረጃ
  3. በመስክ አሰልጣኞች ስልጠና- 2,200 ሰዎች በ20 ከተሞች
  4. በምርጫ ክልል አስፈጻሚዎች እና ዞን አስተባባሪዎች ስልጠና- 3,781 ሰዎች በ20 ከተሞች
  5. የምርጫ ጣቢያ ምርጫ አስፈጻሚዎች ስልጠና - 245,000 ( በአራት ዙር) ደረጃዎች ይከናወናል።

በአራት ደረጃ የሚከናወነው ይህ ስልጠና የሚሰጥባቸው ርእሶች

- የድምፅ መስጫ ቀን ዝግጅት

- ቆጠራ እና ውጤት ገለጻ በምርጫ ጣቢያ ደረጃ

- ውጤት ድመራ ፣ አስተዳደር እና ይፋ ማድረግ በምርጫ ክልል ደረጃ ይሆናሉ። ይህ በየደረጃው የሚደረግ ስልጠና 23 ቀናት ያህል ይፈጃል።

3. የቁሳቁስ እሸጋ እና ስርጭት (ስልጠና እና የድምጽ መስጫ ቀን)

ለስልጠና ቁሳቁስ እሸጋ እና ስርጭት በአጠቃላይ 4 ቀናት ይፈጃል። የድምጽ መስጫ ወረቀት ህትመት ከ10 ቀናት በኋላ የሚናቀቅ ሲሆን ከዚያም በተጨማሪ የድምጽ መስጫ ወረቀት፣ ፎርሞች እና ከሌሎች ተገዝተው የተቀመጡ የድምፅ መስጫ ቀን ቁሳቁሶችን በምርጫ ክልል አከፋፍሎ ማሸግ የድምጽ መስጫ ወረቀት ህትመት ከተጠናቀቀ በኋላ አራት ሳምንታት ይፈጃል።

ከዚህ በተጨማሪ ቦርዱ የትራንስፓርት እቅድ ያዘጋጀ ሲሆን ከመራጮች ምዝገባ ልምድ በመነሳት የፌዴራል ተቋማት፣ የክልል መንግስታት እና የሌሎች አካላት ከፍተኛ ትብብር ይጠይቃል። ይህ የኦፕሬሽን ዝግጅት ቦርዱ በሙሉ ሃይሉ አሟጦ በመጠቀም የሚከናወን ይሆናል።

በዚህም መሰረት 6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ የሚካሄደው በ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ይሆናል። ይህም ሆኖ ድምጽ መስጠት ሂደቱ በተለያዩ ምክንያቶች ሊከናወንባቸው የማይችልባቸው የምርጫ ክልሎች እና የምርጫ ጣቢዎች የሚኖሩ ሲሆን

  1. የመራጮች ምዝገባ ያልተጀመረባቸው ቦታዎች ፣ በጸጥታ ችግሮች
  2. የመራጮች ምዝገባ ተጀምሮ የተቋረጠባቸው ቦታዎች
  3. የመራጮች ምዝገባ ላይ ሂደት ላይ አቤቱታ የቀረበባቸው ወይም ቦርዱ የመራጮች ምዝገባ ሂደቱ ላይ ጉልህ የአሰራር ችግር በማየቱ ማጣራት የወሰነባቸው ቦታዎች በተለያዩ ምክንያቶች (በጸጥታ እና በመራጮች ምዝገባ አቤቱታ) ድምጽ መስጠት ሂደቱ በሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ተግባራዊ ሊሆን የማይችልባቸው የምርጫ ክልሎችን ቦርዱ የለየ ሲሆን እነሱም የሚከተሉት የምርጫ ክልሎች ናቸው።

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል (4 ምርጫ ክልል)

የመራጮች ምዝገባ ያልተጀመባቸው ቦታዎች

  1. መተከል ምርጫ ክልል
  2. ሺናሻ ልዩ ምርጫ ክልል
  3. ካማሽ ምርጫ ክልል
  4. ዳለቲ ምርጫ ክልል

ሶማሌ ክልል (14 ምርጫ ክልል)

የመራጮች ምዝገባ ሂደት ላይ አቤቱታ የቀረበባቸው እና የማጣራት ሂደቱ ላይ የሚወሰኑ

  1. አራቢ የምርጫ ክልል
  2. ደግሃመዶ ምርጫ ክልል
  3. ጎዴ የምርጫ ክልል
  4. ጂግጂጋ 1 የምርጫ ክልል
  5. ጂግጂጋ 2 የምርጫ ክልል
  6. ቀብሪደሃር ምርጫ ክልል
  7. ቀላፎ ምርጫ ክልል
  8. ዋርዴር ምርጫ ክልል
  9. ፊቅ ምርጫ ክልል
  10. ገላዲን ምርጫ ክልል
  11. ደገሃቡር ምርጫ ክልል

የመራጮች ምዝገባ ሂደት በክልሉ መስተዳድር የተቋረጠባቸው

  1. አይሻ ምርጫ ክልል
  2. ኤረር ምርጫ ክልል
  3. ሽንሌ ምርጫ ክልል

ኦሮሚያ ክልል ( 7 ምርጫ ክልል)

የመራጮች ምዝገባ ያልተጀመረባቸው ( በጸጥታ ችግር)

  1. ቤጊ ምርጫ ክልል - ምእራብ ወለጋ
  2. ሰኞ ገበያ ምርጫ ክልል - ምእራብ ወለጋ
  3. አያና ምርጫ ክልል - ምስራቅ ወለጋ
  4. ገሊላ ምርጫ - ምስራቅ ወለጋ
  5. አሊቦ ምርጫ ክልል -ሆሮ ጉድሩ
  6. ጊዳም ምርጫ ክልል- ሆሮ ጉድሩ
  7. ኮምቦልቻ ምርጫ ክልል- ሆሮ ጉድሩ

አማራ ክልል (8 ምርጫ ክልል)

የመራጮች ምዝገባ ያልተጀመረባቸው (በጸጥታ ችግር)

  1. ማጀቴ (ማኮይ) ምርጫ ክልል
  2. አርጎባ ልዩ ምርጫ ክልል
  3. ሸዋሮቢት ምርጫ ክልል
  4. ኤፌሶን ምርጫ ክልል
  5. ጭልጋ 1 ምርጫ ክልል
  6. ጭልጋ 2 ምርጫ ክልል
  7. ላይ አርማጭሆ ምርጫ ክልል
  8. ድልይብዛ ምርጫ ክልል

ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል (4 ምርጫ ክልል)

የመራጮች ምዝገባ ያልተጀመረባቸው (በጸጥታ ችግር)

  1. ዘልማም ምርጫ ክልል
  2. ሱርማ ልዩ ምርጫ ክልል
  3. ዲዚ ልዩ ምርጫ ክልል
  4. ሙርሲ ልዩ ምርጫ ክልል

ሐረሪ ክልል (3 ምርጫ ክልል)

የመራጮች ምዝገባ ከፍተኛ የተዛባ አሰራር የታየባቸው እንዲሁም በህግ የተያዘ ጉዳይ

  1. ጀጎል ልዩ ምርጫ ክልል
  2. ጀጎል መደበኛ ምርጫ ክልል
  3. ጀጎል ዙሪያ እና ሁንደኔ ምርጫ ክልል

ልዩ መግለጫ

በጋምቤላ ክልል ዲማ ምርጫ ክልል እና አኮቦ ምርጫ ክልል ከፍተኛ የመሰረተ ልማት እና የመጓጓዥ ችግር ከፍተኛ በመሆኑ በልዩ ሁኔታ የክልል እና የፌደራል መንግስትን ከፍተኛ እገዛ ይጠይቃል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ግንቦት 14 ቀን 2013 ዓ.ም