Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ኛዉን አጠቃላይ ምርጫ ለመታዘብ ለሲቪል ማህበራት እውቅና የመስጠት ስራውን አጠናቀቀ። 134,109 የአገር ውስጥ ታዛቢዎች ይሰማራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ስራውን አጠናቀቀ። 134,109 የአገር ውስጥ ታዛቢዎች ይሰማራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫን ለመታዘብ ፍላጎት ላላቸው የሀገር ዉስጥ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፍቃድ ለማግኘት ማመልከቻዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ባወጣዉ ማስታወቂያ መሰረት 111 ድርጅቶች እውቅናን ለማግኘት ያመለከቱ ሲሆን ድርጅቶቹ ያቀረቡትን ማመልከቻዎች እና ተያያዥ ሰነዶች በምርጫ ህጉ፣ በወጣዉ ጥሪ እና በመመሪያዉ የተደነገጉትን መስፈርቶች እና ግዴታዎች ያሟሉ ስለመሆኑ፣ እንዲሁም የድርጅቶቹ የማስፈፀም አቅም ተገምግሞ፣ እና በየደረጃዉ የተጓደሉ ሰነዶችን እንዲያሟሉ በማድረግ በመጀመሪያዉ ዙር ካመለከቱ ከ111 ድርጅቶች መካከል 43ቱ ድርጅቶች ወደ ሁለተኛዉ ዙር እንዲያልፉ ተደርጓል፡፡

ወደ ሁለተኛ ዙር ያለፉት 43 ድርጅቶች በምርጫ መታዘብ ስልት (Methodology)፣ የሥልጠና እቅድ(Training Plan) እንዲሁም የታዛቢዎች አመራረጥ(Observers recruitment planning) በተመለከተ በቦርዱ የቅድመ እውቅና ስልጠና (የዓለም አቀፍ ተሞክሮ ታክሎበት) ተሰጥቷቸዉ በመድረኩ ያገኙትን ግብአት በመጠቀም ከላይ የተጠቀሱትን ሦስት የታዛቢነት ስትራቴጂዎችን እንዲያቀርቡ ተደርጎ ከ 43ቱ ድርጅቶች መካከል 36ቱ ስድስተኛዉን አጠቃላይ ምርጫ እንዲታዘቡ ተመርጠዋል፡፡

የተመረጡት 36ቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች 134,109 ታዛቢዎችን ያቀረቡ ሲሆን ከዚህ ዉስጥ፡

=>በሴቶች ጉዳይ ላይ በሚሰሩ 8 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የቀረቡ 61,851 ሴት ታዛቢዎች(46%) ሲሆኑ፣

=>በኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን ስር የታቀፉ 7 ማህበራትን ያካተተ 244 ታዛቢዎች፣ እና

=>በሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮች የምርጫ ሂደትን ለመታዘብ በተመረጠ 1 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት የቀረቡ 100 ታዛቢዎች እና

=>በስሩ 173 ያህል ሲቪል ማህበራትን ያቀፈ የሲቪል ማህበረሰብ ኔትወርክ ይገኙበታል።

በቀጣይ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለተመረጡት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን የሚያዘጋጅ ሲሆን በአጠቃላይ የሚሰማሩትን 134,109 ታዛቢዎችን ለመደገፍ እና ለመከታተልም ስትራቴጂ ነድፏል፡፡

https://nebe.org.et/am/accredited-csos

Share this post