የሥነ ዜጋ እና የመራጮች ትምህርት ለመስጠት እና ምርጫን ለመታዘብ በቦርዱ ፈቃድ የተሰጣቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች
ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዕውቅና አግኝተው በታዛቢነት የተሠማሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት ዝርዝር
ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፍቃድ አግኝተው በመራጮች ትምህርት ላይ የተሠማሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማት ዝርዝር
የሥነ ዜጋና የመራጮች ትምህርት ለመስጠት በቦርዱ ፈቃድ የተሰጣቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች
በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀፅ 124 መሠረት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ መራጮች በቂ ምርጫ ነክ ግንዛቤ የሚያገኙበትን ስልት በመቀየስና የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም የሥነ ዜጋና የመራጮች ትምህርት ይሰጣል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ቦርዱ የሥነ ዜጋና የመራጮች ትምህርት መስጠት እንዲችሉ ህጋዊ ሰውነት ላላቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና የትምህርት ተቋማት፤ የማስተማር ፈቃድ ይሰጣል፡፡
አንድ መራጮችን ለማስተማር የሚፈልግ ድርጅት ፈቃድ እንዲሰጠው ለቦርዱ ሲያመለክት በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 125 መሠረት ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን መስፈርቶች ማሟላት ይጠበቅበታል፡፡
- በህግ ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስ አገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ወይም እውቅና ያለው የከፍተኛ ትምርህት ተቋም መሆኑን፤
- ለመራጮች ትምህርት ያወጣውን መስፈርት የሚያሟላ መሆኑን፤
- ተግባሩን ለመወጣት የሚያስችል ብቃት ያለው መሆኑን፤
- ከማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ገለልተኛ መሆኑን፤
እነዚህ መስፈርቶች ሲሟሉ ቦርዱ ያዘጋጀውን የመራጮች ትምህርት አሰጣጥ ሥነ ምግባር መመሪያ መቀበላቸውን ድርጅቱንና ወኪሎቹን በማስፈረም የማስተማር ፈቃድና መታወቂያ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡
ከላይ የተዘረዘሩትን መስፈርቶች የሚያሟላ ማንኛውም ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት፡-
- ቦርዱ ለዚሁ ያዘጋጀውን የማመልከቻ ቅፅ በመሙላት እና ማስረጃዎቹን በማያያዝ የምርጫው ቀን ቢያንስ 6 ወራት ሲቀረው ለቦርዱ ማቅረብ አለበት።
- የስነዜጋና የመራጮች ትምህርት ለማስተማር የሚያስፈልገውን የገንዘብ መጠን፣ የማስተማር ሥራውን ለማጠናቀቅ የሚፈጅበትን ጊዜ፣ የሰው ኃይል አመዳደቡን፣ እና የማስተማር ሥራውን የሚያካሂድበትን ክልል፣ ከተማ፣ ክፍለ ከተማ፣ ዞን፣ ወረዳና ቀበሌ ያካተተ ዝርዝር እቅድ በማዘጋጀት ከማመልከቻው ጋር አያይዞ ለቦርዱ ማቅረብ አለበት።
- ለሥነዜጋና የመራጮች ትምህርት በመሪነት፣ በአስተባባሪነት፣ በአስተማሪነት እና በመሳሰለው ተግባር የሚያሠማራቸውን ሰዎች ዝርዝር ቦርዱ ባዘጋጀው ቅጽ በመሙላት ተያያዥ ማስረጃዎችን አባሪ በማድረግ ከማስተማር ፈቃድ መጠየቂያ ማመልከቻው ጋር ለቦርዱ ማቅረብ አለበት።
በምርጫ ህጉ አንቀጽ 124(3) መሠረት በቦርዱ ፈቃድ የተሰጣችው ተቋማትና ድርጅቶች የሚሰጥ የሥነ ዜጋና የመራጮች ትምህርት እንዲሁም ስልጠና፣ ቦርዱ በሚያዘጋጃቸው የማስተማሪያ ሰነዶች ላይ መሠረት ያደረገ ይሆናል፡፡ ለተጨማሪ መረጃ የአዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 124 እና 125 እና በዚህ ማስፈንጠሪያ ላይ የሚገኘውን “የመራጮች ትምህርት ፈቃድ አሰጣጥ እና የስነ-ምግባር መመሪያ ቁጥር 04/2012 ዓ.ም” ይመልከቱ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መመሪያ ቁጥር 04ን መሰረት በማድረግ የመራጮች ትምህርት ለመስጠት ለሚፈልጉ ለሲቪል ማህበራት ጥሪ ያቀረበ ሲሆን በጥሪው መሰረት መስፈርቱን አሟልተው ፈቃድ ያገኙ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ስም ዝርዝር የሰነድ ማጣራቱ እንደተጠናቀቀ እዚህ ድህረ ገጽ ላይ የሚቀመጥ ይሆናል፡፡