የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተቋቋመበት አዋጅ 1133/2011 በምርጫ በፖለቲካ ፓርቲዎች እና በስነምግባር አዋጅ 1162/2011 በተሰጠው ስልጣን መሰረት ፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍ እና ቁጥጥር የሚያደርግ ተቋም ነው። በዚህም መሰረት በኦነግ ፓርቲ አመራሮች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት ህጋዊ እና ተደጋጋሚ ጥረቶችን ሲያደርግ እንደነበር ይታወሳል።
በዚህም መሰረት
1. የፓርቲው የተወሰኑ የስራ አስፈጻሚ አባላት ነሃሴ 01 ቀን 2012 ዓ.ም በተጻፈ እና በድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር በተፈረመ ደብዳቤ የድርጅቱን ሊቀመንበር መታገዳቸውን ለቦርዱ አሳውቀው እንደነበር፣ ከዚህም በተጨማሪ የድርጅቱ አመራር ላይ ተከታታይ አቤቱታዎች አስገብተው እንደነበር ይታወሳል። በሌላ በኩል የድርጅቱ ሊቀመንበር መስከረም 02 ቀን 2013 ዓ.ም ድርጅቱ ብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ አድርጎ የፓርቲውን ምክትል ሊቀመንበር፣ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን እንዲሁም የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት እስከሚቀጥለው የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ድረስ ከሃላፊነታቸው ታግደው እንዲቆዩ እንደወሰነ ለቦርዱ አሳውቀዋል።
2. ፖለቲካ ፓርቲ አባላት መኻከል አለመግባባት ሲከሰት እና ለቦርዱ አቤቱታ ሲቀርብለት በአዋጅ ቁጥር 1162/11 አንቀፅ 74 ንዑስ አንቀፅ 6 መሠረት ጉዳዩን ተመልክቶ የውሣኔ ሃሣብ የሚያቀርብ የባለሙያዎች ጉባኤ ለማቋቋም በተሰጠው ስልጣን መሰረት በማድረግ የሁለቱንም ቡድኖች ደብዳቤዎች እና አቤቱታዎች እንዲሁም የውስጥ ህጎች የሚያይ የባለሞያዎች ኮሚቴ ለማቋቋም ውሳኔ አሳልፎ እንደነበርም ይታወሳል፡፡ በዚህም መሰረት በእነ አቶ አራርሶ በኩል ባለሞያ ቢመድቡም ፣ በእነ አቶ ዳውድ በኩል ባለሞያ ለመመደብ ፍቃደኛ ካለመሆናቸውም በላይ የፓርቲው የውስጥ ደንብ መሰረት መጠናቀቅ ያለበት ጉዳይ ነው በማለት መልስ በመስጠታቸው የባሞያዎች ጉባኤ ማቋቋም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
3. በኦነግ አመራር መካከል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የተደረገው የመጀመሪያው የቦርዱ ጥረት ባለመሳካቱ ጉዳዩን ከባለሞያዎች ጉባኤ ይልቅ በራሱ ሊያየው ተገድዷል። በዚህም መሰረት ከሁለቱም ወገን የገቡትን እገዳዎች በማየት እና የገቡ ሰነዶችን በመመርመር እንዲሁም ከሁለቱም ቡድን አመራሮች ጋር እንዲሁም ከስነስርአት እና ቁጥጥር ኮሚቴ አመራር አባላት ጋር ሰፊ ውይይት አድርጓል። በውይይቱም ወቅት ፓርቲው አመራር ቀውስ ውስጥ እንደገባ፣ ለአባላቱ አመራር መስጠት የሚችልበት ሁኔታ ላይ እንዳልሆነ፣ በተለይም ደግሞ ሁለቱም ቡድኖች ያቀረቧቸው እገዳዎች ህጋዊ እንዳልሆኑ ቦርዱ ወስኗል። በዚህም መሰረት የሁለቱም ወገን እገዳ የቀረበባቸው አባላት በነበራችው ህጋዊ ሃላፊነት ላይ እንደሚቆዩ ወሰነ።
በተጨማሪም ሁለቱም አካላት ህጋዊ ሂደቱ የተሟላ ሰነድ ባለማቅረባቸው፣ ፓርቲው ያለበት የአመራር ቀውስ ለመፍታት አለመቻላቸውን በመረዳት ቦርዱ የአመራር መከፋፈሉን ጠቅላላ ጉባኤ በማከናወን የፓርቲው አባላት መሪዎቻቸውን እንዲመርጡ ታህሳስ 08 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ከመወሰኑም በተጨማሪ የጠቅላላ ጉባኤውን ለማመቻቸት ሃላፊነቱንም እንደሚወስድ አሳውቆ እንደነበር ይታወሳል።
4. ከላይ በተጠቀሰው ውሳኔ መሰረት ለሁለቱም አመራር ቡድኖች ቦርዱ ውሳኔ በደብዳቤ ደርሷቸው የመጀመሪያውን ውይይት በቦርዱ አመቻችነት በጋራ ለማከናወን የመጀመሪያውን የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ አባላት ጥሪ ቢደረግላቸውም በድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አራርሶ የሚመራው የስራ አስፈጻሚ ቡድን ቦርዱ በጠራው ስብሰባ ላይ ሲገኝ በአቶ ዳውድ የሚመራው ቡድን ግን “ቦርዱ ይህንን የማመቻቸት ህጋዊ ሚና የለውም” በማለት በውይይቱ ላይ አልገኝም በማለታቸው በቦርዱ የተደረገው ጥረት አሁንም ሊሳካ አልቻለም።
5. ይህ ሂደት በዚህ ላይ እንዳለ ሁለቱም ወገኖች የተለያዩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ሚመለከቱ ማመልከቻዎችን ለቦርዱ ማቅረባቸውን ቀጥለዋል።
6. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥር 19 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው የቦርድ አመራር አባላት ስብሰባ በኦነግ ስራ አስፈጻሚ መከፈልን አስመልክቶ እስከአሁን የተደረጉ ጥረቶችን እና ለመፍታት የወሰዳቸውን እርምጃዎች በዝርዝር መርምሯል። በዚህም መሰረት ቦርዱ እጁ ላይ ባሉት የህግ እና የአስተዳደር መሳሪያዎች በመጠቀም ሊያግዝ የሚችልበት ተጨማሪ አሰራር አለመኖሩን ተረድቷል።
7. በዚህም መሰረት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አባላት፣ የተለያዩ የድርጅቱ መዋቅሮች እና አመራሮች ለችግሩ መፍቻ ሊሆን የሚችለውን ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርጉ ቦርዱ ማሳሰብ እንደሚገባው ወስኗል። በመሆኑም ፓርቲው በመሃከሉ ያለውን አለመግባባት በስራ አስፈጻሚ አመራሮቹ ሊፈታ ባለመቻሉ የተለያዩ የድርጅቱ መዋቅሮች እና አባላት አውቀው ጠቅላላ ጉባኤ እነዲከናወን የሚያደርጉባቸውን ማንኛውንም መንገዶች እንዲጠቀሙ ቦርዱ በጥብቅ ያሳስባል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ጥር 27 ቀን 2013 ዓ.ም