Skip to main content

ቦርዱ ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጋር ምክክር አካሄደ

ግንቦት 20 ቀን 2010 ዓ.ም.

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ “በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚዲያዎች ሚና” በሚል ርዕስ ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጋር ምክክር አደረገ። ቦርዱ ከአውሮፓ ህብረት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የምክክር አውደጥናት ግንቦት 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ተካሂዷል፡፡

የቦርዱ ሰብሳቢ ክብርት ብርቱካን ሚደቅሳ በመክፈቻ ንግግራቸው ሚዲያ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ያላቸው ቁርኝት ከፍተኛ መሆኑን ገልፀው፤ ሚዲያ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ላይ የማይተካ ሚና እንዳለው አብራርተዋል። “በአገራችን የተለያዩ ምርጫዎች ተካሂደዋል። ቀጣይ የምናካሂደው ምርጫ ግን ከነበሩት ምርጫዎች የተሻለ እና ደረጃውን ከፍ ያለ እንዲሆን እየሠራን ነው፣ ሚዲያዎችም ለህብረተሰቡ በተለይ ለመራጩ መረጃ በመስጠት በኩል የላቀ ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል” ብለዋል። የአውሮፓ ህብረት ተወካይ ቴሪ ሌተናል በበኩላቸው ሚዲያ በምርጫ ሂደት ዙሪያ ያለውን ሚና ትልቅ እንደሆነ ገልፀው፤ ሚዲያ ሙሉ የምርጫ ዑደት እንደሚዘግብ እና ቆጠራውንም እንደሚቆጣጠር በመገንዘብ ይህን ታላቅ ኃላፊነት ሙያዊ እና ኃላፊነት በተሞላበት ሥራዎችን በጥንቃቄ መከናወን እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ “ምርጫ እና ሚዲያ“ በሚል ፅሑፍ ያቀረቡት የህግና የሚዲያ ባለሞያው ሰለሞን ጎሹ ምርጫ ለዴሞክራሲ ያለው ሚና ቁልፍ እንደሆነ ገልፀው፤ ምርጫ ስለተከናወነ ብቻ ዴሞክራሲ አለ ማለት እንደማይቻል ተናግረዋል። ምርጫው ዴሞክራሲ የሚያሰፍነው ሚዲያዎቹ ነፃ ሆነው ያለምንም ጫና የምርጫ ዑደቱ ሲዘግቡና ሙያዊ ግዴታቸው ሲወጡ እንደሆነ አብራርተዋል። ሚዲያው በቅድመ ምርጫ እና በምርጫ ጊዜ ተደራሽነቱን አጠናክሮ መረጃዎችን በአግባቡ አግኝቶ የሚዘግብ ከሆነ፤ መረጃውን ለሕዝቡ በማድረስ በድህረ ምርጫ የሚታዩ አለመግባባቶች እና ግጭቶችን መቀነስ እንደሚቻልም ተናግረዋል። ስለሆነም ምርጫ ቦርድ ለሚዲያ አካላት መረጃ በመስጠት በኩል ክፍተቶቹን ለመሙላት በርትቶ መሥራት እንደሚገባው ጠቁመዋል። ሁለተኛ ፅሑፍ  “ዲጂታል ሚዲያ ያለውን ዕድል እና ስጋት” በሚል ርዕስ ያቀረቡት ብርሃን ታዬ ሲሆኑ ሶሻል ሚዲያን ጨምሮ ዲጂታል ሚዲያዎች በዓለም ያለውን ተፅዕኖ በማብራራት በተለይ በምርጫ ጊዜ ኃላፊነት በተሞላበት አኳኃን ትኩረት ተሰጥቶት መሠራት ካልተቻለ ቦርዱ ይህን ጉዳይ መቆጣጠር ስለማይችል ስጋት ሊሆን እንደሚችል እና በአግባቡ ከተጠቀምንበት ግን ለብዙ ህብረተሰብ በቀላሉ ሊደርስ የሚችል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ጥቅም እንደሚኖረው ገልጸዋል።

ውይይቱን የመሩት ሰሎሜ ታደሰ ሲሆኑ በተነሱት ጭብጦች ላይ ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጥያቄዎች እና አስተያየት ተሰንዝረው፤ በፅሑፍ አቅራቢዎቹ ማብራሪያዎች ቀርበዋል። ቦርዱ ለመገናኛ ብዙሃን በሚፈለገው መልኩ ተደራሽ ለመሆን የሚያስችል የአሠራር ማብራሪያ በቦርዱ የኮምዩኒኬሽን አማካሪ ሶልያና ሽመልስ የቀረበ ሲሆን፤ የቦርዱ የማህበራዊ ሚዲያ አድራሻዎች፣ በቃለ መጠይቅ አቀራረብ፣ በቋሚ የምርጫ ሪፖርተሮች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥቷል።
በስተመጨረሻም ባለፉት ስድስት ወራት የተሠሩ ዋና ዋና ሥራዎች ላይ በቦርዱ ሰብሳቢ አማካኝነት ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።

 

Share this post