Skip to main content

በአዲሱ የምርጫና እና የፓለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ላይ ሕዝባዊ ውይይት ተደረገ

ሐምሌ 18 ቀን 2011 ዓ.ም.

በጠቅላይ አቃቤ ህግ ስር በሚገኘው በህግና በፍትህ ማሻሻያ ምክር ቤት የዴሞክራሲ ተቋማት የሥራ ቡድን አዲሱ የምርጫና የፓለቲካ ፓርቲዎች አዋጅን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር በመተባበርና ከተለያዩ የፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመወያየት የተረቀቀውን ህግ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ በትላንትናው ዕለት የዴሞክራሲና የፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለሕዝብ ክፍት የሆነ ውይይት ያዘጋጀ ሲሆን የተለያዩ የፓለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪክ ማህበራት ተወካዮች ተሳትፈውበታል፡፡ በዚህ ውይይት የተለያዩ በህጉ ላይ የተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ የተሰጠባቸው ሲሆን ሁለት ጉዳዮች በዋናነት ሰፊ ውይይትና ክርክር ተደርጎባቸዋል፡፡ የህግ አርቃቂ ባለሞያዎቹ እና የቦርዱ ኃላፊዎችም ለጥያቄዎቹ መልስ የሰጡ ሲሆን የህጉን መነሻ መርሆዎች በዝርዝር ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡

ሁለቱ ከፍተኛ ክርክር የተደረገባቸው ጉዳዮች;

1. አገር አቀፍ ፓርቲ ለመመሥረት 10 ሺህ መመስረቻ ፊርማ ያስፈልጋል የሚለውን ፓርቲዎች 10000 አባላትን ደጋፊ ፊርማ ማሰባሰብ ያስቸግረናል በማለት ተቃመውታል፡፡ የቦርዱ ሰብሳቢ ክብርት ብርቱካን ሚደቅሳ በበኩላቸው አንድ መንግሥት ለመመሥረት የሚወዳደር አገር አቀፍ የፓለቲካ ፓርቲ 10 ሺህ ደጋፊዎችን ማሰባሰብ መቻሉ አስፈላጊና ጫና የማያሳድር ነገር ግን ፓለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን ማህበረሰባዊ መሠረት ለማስፋት የሚረዳ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከ100 ሚልዮን በላይ ዜጎች ባለበት አገር አገር አቀፍ ፓርቲ ለመሆን 10 ሺህ የደጋፊ ፊርማ ማሰባሰብ ካለን የሕዝብ ቁጥርም አንጻር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

2. የመንግሥት ሠራተኞች (ሲቪል ሰርቪስ) ወደ ምርጫ ውድድር በሚገቡበት ወቅት በጊዜያዊነት ከመንግሥት ሥራቸው መልቀቅ አለባቸው የሚለው የህጉን ክፍልም ከፍተኛ ውይይትና ክርክር ተደርጎበታል፡፡ ፓርቲዎች የመንግሥት ሠራተኞችን የምርጫ ፓለቲካ ተሳትፎ ይጎዳል በሚል የተቃወሙት ሲሆን የምርጫ ቦርድ ላፊዎችና የህግ አርቃቂ ቡድኑ በበኩላቸው የመንግሥት ሥራ በፓለቲካ የተነሳ እንዳይጎዳ እንዲሁም በፓርቲና በመንግሥት መቀላቀል የተነሳ ይቀርብ የነበረውን የሃብት አጠቃቀም ችግር እና አቤቱታ ያስቀረዋል በሚል የህጉ አካል መደረጉን ገልጸዋል፡፡ የመንግሥት ሃብት ለምርጫ ስራ እንዳይውል ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ከመሆኑም በተጨማሪ በመንግሥት ሥራ ስም ለምርጫ ቅስቀሳ እና የፓርቲ ፓለቲካ ሃብት እንዳይውል በሚል የተዘጋጀ መሆኑን ማብራሪያ ሰጥተውበታል፡፡ የሲቪል ሰርቪስ አዋጁም በተመሳሳይ እገዳ እንደሚያስቀምጥም ተጠቁሟል፡፡

ከላይ ከተጠቀሱት ከሁለቱ በተጨማሪ በአካል ጉዳተኝነት፣ የሴቶች ተሳትፎን ማጠናከር የመሳሰሉት ግብአቶች ከተሳታፊዎች የተነሱ ሲሆን አንዳንዶቹ የምርጫ ሥርዓቱን ዓይነት የመሳሰሉት ማሻሻያዎች ህገ-መንግሥታዊ ለውጥ የሚልጉ በመሆናቸው ያልተቀየሩ ሲሆን ከዚያ ደረጃ በታች ያሉ ማንኛውንም አስተያየቶች እና ዓለም አቀፍ ልምዶች ከግምት ውስጥ በማስገባት በህጉ ውስጥ ተካተው ለቋሚ ኮሚቴው እንደሚቀርቡ በውይይቱ ወቅት ተገልጸዋል፡፡

Share this post