ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ በትላንትናው ዕለት ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት እና ከገንዘብ ሚኒስትር ጋር በመሆን የጋራ የፕሮጄክት ሰነድ ፈርመዋል
ሰኔ 13 ቀን 2011 ዓ.ም.
ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ በትላንትናው ዕለት ከተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት እና ከገንዘብ ሚኒስትር ጋር በመሆን የጋራ የፕሮጄክት ሰነድ ፈርመዋል። የ40 ሚልዮን ዶላር በጀት ያለው የፕሮጄክት ሰነዱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚቀጥለውን አገራዊ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሃዊና ተአማኒ እንዲሆን የምርጫ ቦርድን አቅም ማሳደግን ጨምሮ ለተለያዩ ከምርጫ ጋር ግንኙነት ላላቸው ተግበራት መሳካት የሚውል ሲሆን ካናዳ፣ ዴንማርክ፣ ፊንላንድ፣ ጀርመን፣ አየርላንድ፣ ጃፓን፣ ኔዘርላንድ፣ ኒውዚላድ፣ ኖርዌይ እና ስዊድን ለበጀቱ አስተዋእጾ አድርገዋል።
የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ፕሮጄክቱ ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ ምርጫ ለማካሄድ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚረዳም በፊርማ ሥነ ስርዓቱ ወቅት ተናግረዋል። የገንዘብ ሚኒስተር ሚኒስትር የተከበሩ አህመድ ሽዴ የኢትዮጵያ መንግሥትን ወክለው በፊርማ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙ ሲሆን አዳዲሶቹ የቦርድ አመራር አባላትም በሥነ ስርዓቱ ላይ ተሳታፊ ነበሩ።