Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአካል ጉዳተኞችን አካታች ያደረገ የምርጫ ሂደትን የተመለከተ አውደ ጥናት አካሄደ

ምርጫ ቦርድ ከተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት /UNDP/ SEEDS PROJECT 2 ባገኘው ድጋፍ ከ ጥቅምት 18-20 ቀን 2017 ዓ.ም. ድረስ የቆየ የአካል ጉዳተኞች በምርጫ ወቅት ሊኖራቸው የሚገባ ፍትሃዊ ተካታችነት የሚዳስስ አውደ ጥናት አካሄደ። አውደ ጥናቱ አካል ጉዳተኞችን ማእከል ያደረገ አሠራርን በምርጫ ሂደቶች እና ሥራዎች ውሰጥ ማቀድን እና አሁን በመተግበር ላይ ያሉ የምርጫ አሠራሮች ለአካል ጉዳተኞች ያላቸውን ተደራሽነት ለመገምገም የሚያስችል እውቀት እና ክህሎትን ለማሳደግ ያለመ ነበር።

በ አውደ ጥናቱ ላይ የመክፈቻ ንግር ያደረጉት የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት /UNDP/ ሪዘደንት ተወካይ ዶ/ር ሳሙኤል ዶ አካታችነት የማህበራዊ ፍትሃዊነት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ለዘላቂ እድገት ወሳኝ በመሆኑ የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት /UNDP/ አካታች የሆነ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር በቁርጠኝነት ይሠራል ከነዚህም ተግባራቱ አንዱ የአካል ጉዳተኞች በምርጫ ወቅት ተደራሽ እንዲሆኑ ማስቻል በመሆኑ ይህንን ሥልጠና እንዲከናወን የደገፉት ከዚህ መሰረታዊ የድርጅታቸው እምነት በመነሳት መሆኑን አውስተው የዚህ አውደ ጥናት ተሳታፊዎች አካል ጉዳተኞች በምርጫ የሚኖራቸውን ተሳትፎና ተደራሽነት ለመተግበር በሚደረግ ጥረት ውስጥ የለውጥ ዘዋሪዎች እንደሚሆኑ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡

ከዚህም በመቀጠል የአውደ ጥናቱን ዓላማ አፅንኦት ሰተው ያብራሩት የምርጫ ቦርድ የቦርድ አባል ብዙወርቅ ከተተ አውደ ጥናት ትኩረት ያደረገው በምርጫ እና አካል ጉዳተኞች ላይ ሲሆን ይህን አውደ ጥናት ለየት የሚያደርገው መጪውን ምርጫ ታሳቢ በማድረግ ክፍተታችን የት ላይ እንደሆነ በመረዳትና የት ላይ ይበልጥ መሥራት እናደለብን ማሳየት የሚያስችል መሆኑና የአካል ጉዳተኞችን ተደራሽ ያደረገ አሠራርን ለመተግበር እንድንችል አውደ ጥናቱ እውቀታችንን ከማሳደጉም በተጨማሪ የሕግ ማእቀፎቻችን እና የምርጫ ሂደቶቻችንን በመመልከት ተግባራዊ ፍተሻ ለማድረግ እንደሚያስችል ገልፀው የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት /UNDP/ ይህንን የ3ት ቀን አውደ ጥናት እንዲዘጋጅ በማገዙ አመስግነዋል፡፡

አውደ ጥናቱ የተሰጠው Building Resources in Democracy Governance and Election/ BRIDGE/ በተባለ ዓለም ዐቀፍ ተቋም አማካይነት ሲሆን በአውደ ጥናቱ ላይ ከምርጫ ቦርድ የተውጣጡ የሥራ ክፍል ኃላፊዎች፤JCPP፣ የአካል ጉዳተኞች ምዘና አማካሪዎች/ The Disability Assessment Consultants/፣ የGESI ቡድን እና ከአካል ጉዳተኞች ምዘና CSO/EHRC አማካሪ ቡድን የተውጣጡ አባላት ተሳትፈዋል ።

አውደ ጥናቱ የእኩል ተደራሽነትን የተመለከቱ ዓለም አቀፍ ሕጎችና ማእቀፎችን፤ በምርጫ ሂደት ውስጥ ተደራሽነትን በተመለከተ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችን፤ የአካል ጉዳተኞች የምርጫ ተደራሽነት በማሳደግ ረገድ ባለድርሻ አካላት ስለሚኖራቸው ሚና፤ አካል ጉዳተኞች በምርጫ ተሳትፎ ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን መሰናክሎች በመለየት መሰናክሎች ለመፍታት መተግበር ስላለባቸው ስልቶች፤ የምርጫ አካታችነት ኦዲት እና አካል ጉዳተኞችን አካታች ለማድረግ የሚያስችል የድህረ ምርጫ ጊዜ እቅድ- ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀትን የተመለከቱ ፅንሰ-ሃሳቦችና የሌሎች ሀገሮች ጥሩ ተሞክሮዎች ተዳሰውበታል፡፡

በአውደ ጥናቱ የመዝጊያ መርኃ ግብር ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት UNDP ምክትል ሪዘደንት ተወካይ ቻሩ ቢስት እንደገለፁት አካትችነትና ዲሞክራሲያዊ ምርጫን በተለይም የአካል ጉዳተኞችን ፍትሃዊ ተሳትፎን ያገናዘበ እና ከዚህም ጋር ተያይዞ ያሉ ተግዳሮቶችን ለማስወገድ የሚደረጉ ጥረቶችን በተመለከተ ሁሉም ነገር በአንድ ጀንበር የሚለወጥ ጉዳይ ስላልሆነ ምርጫ ቦርድ የአካል ጉዳተኞችን የምርጫ ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያደርገውን ጥረት ለማገዝ አሰተዋፅ ማድረጋችንንም እንቀጥላለን ብለዋል፡፡

የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልእክት ምንም እንኳን አካል ጉዳተኞችን አካታች በማድረግ ሂደት ላይ ቦርዱ ብዙ ሊሠራቸው የሚገባ ቀሪ የቤት ሥራዎች እንዳሉብን ቢያውቅም በተለይም ቦርዱ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞችን በሚቀጥርበት ጊዜ ለሴቶች እና ለአካል ጉዳተኞች ቅድሚያ ለመሥጠት ነገሮችን ታሳቢ በማድረግ እየሠራ ከመሆኑም ባሻገር የምርጫ ቦርድ የምርጫ ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹና ተደራሽ እንዲሆኑ፤ በመራጮች ምዝገባና በምርጫ ዕለት ቅድሚያ እንዲያገኙና አካል ጉዳተኞች ቦርዱ በሚያዘጋጅላቸው ረዳት ወይም የራሳቸውን ረዳትም ይዘው በመምጣት በምርጫ እንዲሳተፉ የተቻለውን ጥረት እያደረገ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን ቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሴትና የአካል ጉዳተኞች አባላት ተሳትፎ ከፍ እንዲል ለማገዝ በአመራርና በአባልነት ያሉ የአካል ጉዳተኞችንና ሴቶችን ቁጥር መሰረት ያደረገ የመንግስት ገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል፡፡

የዚህ አውደ ጥናት መዘጋጀት ዋነኛ ዓላማም በእውቀት እና በጥናት ላይ ላይ የተመሰረተ የአካል ጉዳተኞችን የምርጫ ተካታችነትን በተሳካ ሁኔታ ለመተግበር ምርጫ ቦርድ ካለው ጥረት ጋር የተያያዘ እንደሆነ የቦርዱ ሰብሳቢ አውስተው በተጨማሪም አውደ ጥናቱ በተሳታፊዎች መሀከል የልምድ ልውውጥ ለማድረግ፤ለቀጣይ ተግባራት በባለድርሻ አካላት መሀከል ጥምረት ለመመስረትና የአካል ጉዳተኞችን የምርጫ ተሳትፎ በመተባበር በተሳካ ሁኔታ ለመተግበር ወደፊት ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥር ያላቸውን እምነት በመግለፅ አውደ ጥናቱን ለማዘጋጀት የገንዘብ ድጋፍ ያደረገውን የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት /UNDP/፤ አውደ ጥናቱን ላስተባበረውን የምርጫ ቦርድ የሥራ ክፍል እና በአውደ ጥናቱ ለተካፈሉ ተሳታፊዎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በመጨረሻም በአውደ ጥናቱ ለተካፈሉ ተሳታፊዎች የምስክር ወረቀት ከተሠጠ በኃላ መርኃ ግብሩ ተጠናቋል፡፡

Share this post