የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 65 መሰረት የፓለቲካ ፓርቲዎችን ምዝገባ እና ድጋሚ ምዝገባ ሲያከናውን እንደነበር ይታወቃል። በዚህም መሰረት ምዝገባቸው የታደሰላቸው ፓርቲዎች እንዳሉ ሁሉ ምዝገባ መስፈርቱን ያላሟሉ ከ27 በላይ ፓርቲዎችን መሰረዙ ይታወሳል። በህጉ መሰረትም በቦርዱ ውሳኔ ቅር የተሰኙ የተለያዩ ፓርቲዎች ወደፍርድ ቤት በመሄድ ክርክር ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ከነዚህ ፓለቲካ ድርጅቶች መካከል

1. ኦሮሞ ኦቦ ነጻነት ግንባር ( ኦአነግ)

2. የኦሮሞ አንድነትና ዴሞክራሲ የፌዴራል የሰላም ለውጥ ( ኦአዴፌሰለ)

3. የኦሮሞ ነጻነት አንድነት ግንባር ( ኦነአግ)

4. ኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ህብረት ( ኦዳ)

የተሰኙት ፓርቲዎች ቦርዱ ላይ ባቀረቡት አቤቱታ ፍርድ ቤቱ ቦርዱ የመሰረዝ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት የመሰማት መብት ለፓርቲዎቹ መስጠት ነበረበት በማለት ቦርዱ ውሳኔውን ከመወሰኑ በፊት ለፓርቲዎቹ የመሰማት መብት በመስጠት መሆን ይገባል ሲል ፍርድ ቤቱ ወስኗል። በፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሰረትም ቦርዱ ለአራቱም ፓርቲዎች የመሰማት እድልን ሰጥቷል። ፓርቲዎቹም በተሰጣቸው እድል መሰረት ምላሻቸውን ያቀረቡ ቢሆንም ዝቅተኛው ህጋዊ የአባላት ፊርማ 35 በመቶ በላይ መሆን ሲኖርበት አሁንም 35 በመቶ ህጋዊ መስራቾች ፊርማን አሟልተው አለማቅረባቸው በድጋሚ ስለተረጋገጠ ቦርዱ እነዚህኑ ፓርቲዎች ከምዝገባው ሂደት መውጣታቸውን እንዲሁ፣ በአዋጅ 1162/2011 ዓ.ም በተደነገገው መሰረት የፓርቲ መሰረዝ ወይም መፍረስ ውጤትን አስመክቶ የተደነገገው ተግባራዊ እንዲሆን ወስኗል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

 

ማስታወቂያ
ታህሳስ 01 ቀን 2014 ዓ.ም