የኢትዮጲያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዓለም ዐቀፍ የፀረ-ፆታዊ ጥቃትና የአካል ጉዳተኝነት ቀንን አስመልክቶ ሁለት ተከታታይ የምክክር መድረኮችን አከናወነ
የኢትየጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአካታችነት እና ስርአት ጾታ የስራ በዚህ ሳምንት ሁለት ተከታታይ ሁነቶችን አካሂዷል፡፡ ሀሙስ ታኅሳስ 01 ቀን 2013 ዓ.ም የተካሄደው የምክክር መድረክ ዓለም ዐቀፍ የፀረ-ፆታዊ ጥቃት ቀንን የተመለከተ ሲሆን፤ የተለያዩ ፓርቲዎች ተወካዮችና የሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች ተሳትፈውበታል፡፡ የቦርድ አመራር በሆኑት አቶ ውብሸት አየለ የመክፈቻ ንግግር የተከፈተው መድረክ፤ የምርጫና የሥርዓተ ፆታ አማካሪ በሆኑት ጨረር አክሊሉና የኢትዮጲያ የሴቶች ማኅበር ተወካይ በሆኑት ኅብረት አባሆይ የፆታዊ ጥቃትን ከዓለም ዐቀፍ ተሞክሮ አንጻር የሚያሳዩ ጽሑፎች የቀረቡበት ሲሆን በምርጫ ዑደት ጊዜ የሚያጋጥሙ ፆታዊ ጥቃት ምን መልክ አላቸው የሚለው በዋና አጀንዳነት ተነስቶበታል። በቀረበው ጽሑፍ ላይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቦርድ አመራር በሆኑት ብዙወርቅ ከተተ፣ እና በጽሑፍ አቅራቢዎች መሪነት ውይይት የተካሄደ ሲሆን ከተሳታፊዎች የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተውበታል፡፡ በዛሬው ዕለት የተካሄደው ሁለተኛው መድረክ ዓለም ዐቀፍ የአካል ጉዳተኝነት ቀንን የተመለከት ሲሆን፤ የቦርዱ አመራር በሆኑት ብዙወርቅ ከተተንና ዶ/ር አበራ ደገፋን ጨምሮ በተጋባዥ እንግዶች ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ሃሳቦች ቀርበውበታል፡፡ ከመድረኩ ተሳታፊዎች ከዚህ በፊት በምርጫ ወቅት ያጋጥሙ የነበሩ ችግሮች በዝርዝር የቀረቡ ሲሆን ቀጣዩን ምርጫ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ለማድረግ ቢካተቱበት ያሏቸውን አስተያየቶች ተሰጥተውበታል፡፡
የቦርድ አመራር አባል የሆኑት ብዙወርቅ በሁለቱም ቀን በተደረጉት የምክክር መድረኮች ላይ በቦርዱ የተደረጉት የሕግ ማሻሻዎች የሴቶችን ተሳትፎ ከማሳደግና ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታዎችን ከመፍጠር አንጻር ልዩ ትኩረት እንደተደረገባቸው በመግለጽ፤ በዐዋጁ አልተካተቱም ተብለው የታሰቡትን ከተለያዩ መድረኮች በተሰበሰቡ ምክረ ሃሳቦችን በመጨምር በመመሪያው እንዲካተቱ መደረጉን አስረድተዋል። የአካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንዲሟሉ ከተደረጉ ቁሳቁሶች ውስጥ የተሻሻለውን ዐዋጅ በኦዲዮና በብሬል ተዘጋጅተው በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን ተገልጿል። ከዚህም በተጨማሪ በምርጫ ዑደቱ ተሳታፊ ለሚሆኑ አካላት ቦርዱ የተለያዩ ሥልጠናዎችን እየሰጠ እንደሚገኝና ተመሳሳይ መድረኮችም እንደሚዘጋጁ ቃል ገብተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ