Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቀድሞ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ንብረት እንዲያጣሩ ሁለት ኦዲተሮችን ሾመ

ሰኔ 6 ቀን 2012 ዓ.ም.

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሰረት ጥር 20 ቀን 2012 ዓ.ም ኢሕአዴግ እንዲፈርስ እንዲሁም የቀድሞ ሶስቱ የግንባሩ አባላት ወራሽ የሆነው ብልጽግና ፓርቲ እና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሐት) በስድስት ወር ውስጥ የንብረት ክፍፍል ተጠናቆ እንዲያቀርቡ ክፍፍሉም የሶስት ፓርቲዎች ወራሽ የሆነው ብልፅግና የሃብቱን ሶስት አራተኛ (3/4) በራሱ ህጋዊ እውቅና ያለው ህወሃት አንድ አራተኛ ( ¼) እንዲወስዱ መወሰኑ ይታወሳል፡፡ በውሳኔውም ፓርቲዎቹ የጋራ ንብረት አጣሪ ሾመው የባለመብቶችን (creditors) መብት እንዲጠበቅ እንዲሁም በተገለጸው ቀመር መሰረትም የንብረት ክፍፍሉ እንዲፈጸም ወስኖ አሳውቆ ነበር፡፡

በሌላ በኩል የብልጽግና ፓርቲ የንብረት ክፍፍሉ እያንዳንዱ ፓርቲ በተናጠል በነበረው የአባላት ብዛት ላይ የተመሰረተ እንጂ በእኩልነት ሊሆን አይገባም የሚል አቤቱታ ያቀረበ ሲሆን ቦርዱ የሃብት ክፍፍሉን የወሰነው የፓርቲው ህገደንብ “ሁሉም ፓርቲዎች በግንባሩ የጋራ ንብረት እኩል የመጠቀም መብት አላቸው” ሲል ያስቀመጠውን መሰረት በማድረግ መሆኑን ገልጾ ሆኖም ግን ብልጽግና ከዚህ የተለየ ውጤት ሊያስከትል የሚችል ማስረጃ ወይም ሰነድ ካለው ለአጣሪው ማቅረብ እንደሚችል ተገልጾለታል፡፡

የመፍረስ ውሳኔው ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ ሁለቱም ወገኖች የሚስማሙበት አንድ የጋራ አጣሪ እንዲመርጡ ለማስቻል የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ ስለሆነም ቦርዱ ብልጽግና ፓርቲ እና ህወሃት በየበኩላቸው የመረጧቸው አንድ አንድ የሂሳብ አጣሪዎች በጋራ በመሆን የንብረት ማጣራት ስራውን እንዲያከናውኑ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ በዚህም ውሳኔ መሰረት የንብረት ማጣራቱን እንዲያደርጉ የተመረጡት ድርጅቶች የጋራ የስራ እቅድ፣ የጊዜ ሰሌዳ፣ ስራውን የሚያከናውኑበት ቦታ፣ ሁኔታ እና የስራ ህግጋት ለቦርዱ እንዲያቀርቡም በደብዳቤ ተገልጾላቸዋል፡፡ የንብረት ማጣራቱ ሂደት ሙሉ ወጪ በፓርቲዎቹ የሚሸፈን ሲሆን ቦርዱ ሂደቱ የሚደርስበትን ደረጃ በየጊዜው ለህዝብ የሚያሳውቅ ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

Share this post