ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ በኢትዮጵያ ውስጥ በፖለቲካ ፓርቲነት ለመንቀሳቀስ የሚችለው በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሠረት በቦርዱ ተመዝግቦ የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ሲያገኝ ብቻ ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ማንኛውም የፓለቲካ ፓርቲ ለማቋቋም የሚፈልጉ የዜጎች ስብስብ ለቦርዱ ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ እንዲሰጣቸው ማመልከት ይችላሉ፡፡ ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ ያገኘ የፖለቲካ ፓርቲ፤ ጊዜያዊ ፈቃዱን መጠቀም የሚችለው በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 66 መሠረት ለሦስት ወራት ብቻ እና ፓርቲውን ለማስመዝገብ የሚያስፈልጉ ተግባራትን ለማከናወን ብቻ ይሆናል፡፡ ሆኖም አመልካቾች በቂ ምክንያት ያቀረቡ እንደሆነ ጊዜያዊ ፈቃዱ ለተጨማሪ ሦስት ወራት ሊራዘም ይችላል፡፡
በፓርቲነት ለመመዝገብ ስለሚቀርብ ማመልከቻ
ማንኛውም የፓለቲካ ፓርቲ የምዝገባ ማመልከቻ
- በፖለቲካ ፓርቲው መሪ ተፈርሞ የቀረበ መሆን አለበት
- የሚከተሉትን ሰነዶች አያይዞ ማቅረብ አለበት
- የፓርቲው መጠሪያ ሙሉ ስም እና አህፅሮተ ስም
- የፓርቲው ዓርማ
- የፓርቲው ዓላማ
- የፓርቲው ንብረትና የገቢ ምንጭ
- የፓርቲው የተመሰረተበት ቀን እና ዓመተ ምህረት
- የፓርቲው ዋና መሥሪያ ቤት እና ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች አድራሻ
- የየመተዳደሪያ ደንቡ አወጣጥ ሥርዓት
- በመስራች ጠቅላላ ጉባኤ የጸደቀ የፓርቲው የመመስረቻ ጽሑፍ
- ፕሮግራም
- ዓላማው አድርጎ የያዘውን የፖለቲካ እምነት የሚቀርጽበት በፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ የፀደቀ የፖለቲካ ፕሮግራም
- የመተዳደሪያ ደንብ
- የአባላት ቅበላና ስንብት ሁኔታ
- የአባላቱ መብትና ግዴታ
- የፖለቲካ ፓርቲው ልዩ ልዩ አካላት፣ የሚመረጡበት ሥርዓት፣ የአገልግሎት ዘመን እና የሥራ ኃላፊነታቸው
- የአባልነት መዋጮ ዓይነትና አከፋፈል እንዲሁም አባላቱ በፓርቲው ሥራ ውስጥ የሚኖራቸው ተሳትፎ
- የፓርቲው የስብሰባ እና የውሳኔ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት
- በአባላቱ ላይ ስለሚወሰድ የሥነ ሥርዓት እና የሥነ ምግባር እርምጃ
- የጠቅላላ ጉባኤ አባላትን ቁጥር ቢያንስ በአዋጅ ቁጥር 1163/2011 መሠረት ፓርቲ ለመመስረት ከተቀመጠው ከዝቅተኛው የመስራች አባላት ቁጥር 5 በመቶ በማድረግ የሚወስን ድንጋጌ
- የፖለቲካ ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ቢያንስ በሦስት አመት አንድ ጊዜ መካሄድ ያለበት መሆኑን የሚገልጽ ድንጋጌ
- የፓርቲው ቅርንጫፎች አወቃቀርና አሠራርን ጨምሮ የፓርቲውን መዋቅራዊ አደረጃጀትና የስልጣን ተዋረድ
- የፓርቲውን ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ የሚፈልጉ ጉዳዮችን ዝርዝር
- የፖለቲካ ፓርቲው ከሌላ ፓርቲ ወይም ፓርቲዎች ጋር ውህደት፣ ቅንጅት ወይም ግንባር የሚፈጥርበት፥ እንዲሁም ፓርቲው የሚፈርስበትን የውሳኔና የድርጊት ሂደቶች
- የፓርቲው አባላት ለአገር አቀፍና በየደረጃው ላሉ አገራዊ ምርጫዎች የሚታጩበት ሥርዓት
- የፖለቲካ ፓርቲው የሰው ኃብት፣ የፋይናንስ እና የኦዲት አስተዳደር ስርአት አሰራር
- የፓርቲውን ገንዘብና ንብረት አስተዳደር ስርአት፣ የገቢ ማስገኛ አሰራር እና በነዚህ ጉዳዮች ላይ ለመወሰን ሥልጣን ያለውን አካል ወይም ኃላፊን የሚገልጽ ድንጋጌ
- የፖለቲካ ፓርቲው የውስጥ አለመግባባቶች አፈታት ሥርዓት
- ማንኛውም አባል እኩል ድምፅ ያለው መሆኑን የሚገልጽ ድንጋጌ
- የፖለቲካ ፓርቲ አባል በዜግነቱ የተረጋገጠለትን መብት የሚቀንስ ወይም የተጣለበትን ግዴታ የሚሽር አለመሆኑ
- የፓርቲው አመራሮችና በየደረጃው ያሉ ኃላፊዎች አመራረጥ ግልጽ፥ ነጻና ፍትሃዊ እንዲሁም በሚስጥር በሚሰጥ ድምፅ መንገድ የሚመረጡ መሆናቸውን መደንገግ
- በማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ለኃላፊነት ቦታ የሚደረጉ ምርጫዎች የጾታ ተዋጽኦን ያገናዘቡ መሆናቸው
- ፕሮግራሙንና የመተዳደሪያ ደንቡን የሚያፀድቅበትንና የሚያሻሽልበትን እንዲሁም ስብሰባ የሚያካሂድበትን ሥነ ሥርዓት በመተዳደሪያ ደንቡ ውስጥ ስለመወሰኑ
- በመተዳደሪያ ደንቡ በሚወሰነው መሠረት የፖለቲካ ሥራውን የሚመሩ፣ ውሳኔ የሚሰጡ እና የሚያስፈፅሙ የአመራር አካላት መኖራቸው
- በአገር አቀፍ ደረጃ፣ በክልልና ከክልል በታች ቅርንጫፎች ያሉት የፖለቲካ ፓርቲ በቅርንጫፎቹ መካከል ያለውን ግንኙነትና የሥልጣን ተዋረድ በመተዳደርያ ደንቡ መደንገጉ
- የፖለቲካ ፓርቲው ኃላፊዎች ስምና አድራሻ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲው ኃላፊዎች በኃላፊነት ለመሥራት መስማማታቸውን የሚያስረዳ በፊርማቸው የተረጋገጠ ሰነድ
- መስራቾች የፈረሙበትና ለሕዝብ በይፋ የሚገለጽ ሰነድ
- የፖለቲካ ፓርቲው ኃላፊዎች በፓርቲው የመተዳደሪያ ደንብ መሠረት ነጻና ዴሞክራሲያዊ በሆነ ምርጫ የተመረጡ መሆኑን የሚገልጽ ሰነድ
- የምዝገባ ሰነዶች አምስት አምስት ቅጂ ከምዝገባ ማመልከቻው ጋር ተያይዞ ማቅረብ
- የምዝገባ የአገልግሎት ክፍያ የከፈለበት ደረሰኝ ከምዝገባ መጠየቂያ ማመልከቻው ጋር አያይዞ ማቅረብ
መመዝገብ ስለማይችል የፖለቲካ ፓርቲ
- የመረጠው ስም፣ አሕጽሮተ ስም፣ አርማ ወይም የመለያ ምልክት ከሀገሪቱ ባህልና የሥነ ምግባር እሴቶች አኳያ ተቀባይነት የሌለው ከሆነ
- የመረጠው ስም፣ አሕጽሮተ ስም፣ አርማ ወይም የመለያ ምልክት በሌላ ፓርቲ የተያዘ አለመሆኑ፣ ወይም ከሌላ ፓርቲ ስም፣ አሕጽሮተ ስም፣ አርማ ወይም የመለያ ምልክት ጋር መራጮችን ሊያሳስት በሚችል ደረጃ የማይቀራረብ ከሆነ
- የመረጠው ስም፣ አሕጽሮተ ስም፣ አርማ፣ የመለያ ምልክት፣ የመመስረቻ ጽሑፍ ወይም የመተዳደሪያ ደንብ በዘር፣ በኃይማኖት እና በመሳሰሉት ልዩነቶች ላይ የተመሰረተ ጥላቻና ጠላትነት በዜጎች፣ በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና በሕዝቦች መካከል በማስፋፋት ጦርነትና ግጭት መፍጠርን ዓላማ ያላደረገ ወይም ሰዎችን በዘር፣ በኃይማኖት ወይም በማንነት ላይ ተመስረቶ ከአባልነት ወይም ከደጋፊነት የማያገል ከሆነ
- ዓላማውን በትጥቅ ለማራመድ ያልተደራጀ ከሆነ
- የውጭ ሀገር ዜጎች አባል ያልሆኑበት የፓለቲካ ድርጅት ከሆነ
- ህገወጥ ዓላማ ለማካሄድ ያልተቋቋመ የፓለቲካ ድርጅት ከሆነ
በፖለቲካ ፓርቲነት ለመመዝገብ ስለማይችል ድርጅት ወይም ማህበር
- በንግድ ህግ ወይም በፍትሐብሔር ህግ ወይም አግባብ ባላቸው ሌሎች ህጎች መሠረት፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሥራዎችን ለማከናወን የተቋቋሙ ማሕበሮች ወይም ድርጅቶች
- ዓላማቸው ትርፍ ለማግኘት ያልሆነ ወይም ለበጎ አድራጎት ተግባር የተቋቋሙ ማሕበራት ወይም ድርጅቶች
- የብዙኃን መገናኛ፣ የሠራተኛ እና የሙያ ማሕበራት
- የመረዳጃ ማሕበራት
- የሃይማኖት ድርጅቶች
- ዕድርና ዕቁብን የመሳሰሉ ማሕበራዊ ተቋሞች
ዝርዝር መረጃ ለማግኘት አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ከአንቀፅ 66 እስከ 70 ይመልከቱ፡፡