Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ከፌዴራልና ከክልል የመገናኛ ብዙኃን ለተውጣጡ ጋዜጠኞች ሥልጠና ሰጠ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ከፌዴራልና ከክልል የመገናኛ ብዙኃን ለተውጣጡ የዜና ክፍል ኃላፊዎች፣ አርታኢያን እና ጋዜጠኞች በገለልተኛ እና ሚዛናዊ የሚዲያ ዘገባ እና ኃቅን (እውነታን) በማረጋገጥ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የአንድ ቀን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጠ።

በሥልጠናው የመክፈቻ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ ምርጫ ለሀገራችን ዲሞክራሲ ማበብ ዋና የማዕዘን ድንጋይ በመሆኑ የመገናኛ ብዙኃን የምርጫ ሂደት አዘጋገብ ከስሜት እና ከወገንተኝነት የፀዳ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የምርጫ ነክ ዘገባዎች ገለልተኛ፣ ሚዛናዊ፣ ፍትሃዊ፣ አካታች፣ አስተማሪና ተሞጋች መሆን እንደሚገባው የሚያሻማ ጉዳይ አይደለም ያሉት ወ/ሮ ሜላትወርቅ መገናኛ ብዙኃን ዲሞክራሲን የሚያጎለብቱ ምርጫ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በተጠና አግባብ አጀንዳ ቀርፀው በተለይ የመራጩን ግንዛቤ በተከታታይ ሊያሳድጉ እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ያለ መገናኛ ብዙኃን ንቁ ተሳትፎ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሊታሰብ አይችልም ያሉት ወ/ሮ ሜላትወርቅ መገናኛ ብዙኃን መራጮች እውቀት ላይ የተመሠረተ ምርጫ እንዲያካሂዱ ስለፓርቲዎች፣ ፖሊሲዎቻቸው፣ ስለ እጬዋቻቸው እና ስለ ምርጫ ሂደት በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ተግተው መሥራት ይገባቸዋል ብለዋል።

አንድ ቀን በቆየው ሥልጠና በምርጫ እና ከምርጫ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ገለልተኛ የሚዲያ ዘገባ ጽንሰ ሃሳብና አተገባበርን በተመለከተና በሚዲያ የተዘገቡ ጉዳዮችን ኃቅ(እውነታን) ለማረጋገጥ በሚረዱ ጉዳዮች ዙሪያ ገለጻ እና የተግባር ልምምድ ተካሂዷል፡፡

በሥልጠናው የመገናኛ ብዙኀን ምርጫ ፍትሃዊ፣ ሚዛናዊ እና ትክክለኛ እንዲሆን የሚያበረክቱት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ፤ ምርጫ ነክ ዘገባዋችን ሲሠሩ በስነምግባር እና ሙያዊ መርሆችን ጠብቀው እንዲሠሩ አፅንኦት ተሰጥቶት ሰፊ ውይይት ከተደረገ በኋላ ሥልጠናው የመርኃ ግብሩን ዓላማ በማሳካት ተጠናቋል፡፡

Share this post