Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ2016 ዓ.ም. በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2017ዓ.ም. በጀት ዓመት ዕቅድን ከቦርዱ የአምስት ዓመት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ አንጻር የቃኘ መድረክ አካሄደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከመስከረም 28 እስከ ጥቅምት 03 ቀን 2017 ዓ.ም የ2016 ዓ.ም. በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እና የቦርዱን የ2017 ዓ.ም. በጀት ዓመት ዕቅድን ከቦርዱ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ጋር የማሰናሰልና እንዲሁም በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ቀሪና ድጋሚ ምርጫ ላይ የተገኙ ልምዶች የተዳሰሱበት መድረክ አካሄደ። የቦርዱ አመራር አባላት፣ በዋናው መሥሪያ ቤቱ የሚገኙ የቦርዱ የሥራ ክፍል ኃላፊዎች፣ የቦርዱ የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ በቀሪና በድጋሚ ምርጫ ላይ የክትትል ቡድን አባላት የነበሩ የቦርዱ ባለሞያዎች እንዲሁም ሌሎች የዋና መሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች የተሣተፉበትን መድረክ በንግግር የከፈቱት የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ውብሸት አየለ ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም ይኽን ስድስት ቀን የሚወስደውን መድረክ ከተጠናቀቀው በጀት ዓመት ግምገማና የተያዘውን በጀት ዓመት ዕቅድ ከቦርዱ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ጋር ከማናበብ ባሻገር እርስ በርስ በደንብ ለመተዋወቂያና መተማመንን ለማጎልበት እንዲሁም የአመራር ብቃታችን እንዴት እንደሚዳብር በነፃነትና በዕውቀት የምንወያይበትና አቅጣጫ የምናስቀምጥበት መሆን እንደሚገባው በአጽንዖት ተናግረዋል።

በመድረኩ የቦርዱን የ2017 ዓ.ም. በጀት ዓመት ዕቅድን ከቦርዱ አምስት ዓመት የስትራቴጂያዊ ዕቅድ አንጻር የተገመገመና የዕቅዱም የክትትልና የግምገማ ሥርዓት የተዋወቀ ሲሆን፤ በተጨማሪም በሰኔ 2016 የተደረገው የ6ኛው የጠቅላላ ምርጫ ቀሪና ድጋሚ ምርጫ ላይ የተወሰዱ መልካም ተሞክሮችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ተተችተውበታል። የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድም በ2016 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ላይ ከተስተዋሉ ክፍተቶችና ተገማች ከሆኑ ተግዳሮቶች አንጻር ከአስፈጻሚዎቹ የቦርዱ የሥራ ክፍል ኃላፊዎችና ከክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊዎች ጋር በመገምገምገም የመፍትሔ አቅጣጫ ተሰጥቶባቸዋል።

ስድስት ቀን የወሰደውን የግምገማና የክለሳ፤ እንዲሁም የመማማሪያ መድረክን በንግግር የዘጉት የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ሲሆን፤ በንግግራቸውም ወርክ ሾፑ (መድረኩ) እንዲሳካ የላቀ ሚና ለነበራቸው የአዘጋጅ አስተባበሪ ኮሜቴ አባላት እና መድረኩን ስፖንሰር ላደረገውን የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ከፍተኛ አድናቆታቸውን እና ምስጋናቸውን ገልጸው፤ ቦርዱ ውጤታማ ሥራ እንዲሠራ የሚደረጉ ጥረቶች በአንድ ጀምበር የምናሳካው ባይሆንም በመድረኩ ግን ለረጅሙ ጉዞ የሚሆን በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ግብዓት መሰብሰቡንና ተስፋ ሰጪ ውይይት በመድረኩ ላይ እንደነበር ተናግረዋል።

Share this post