የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች አካታችነትን በተመለከተ ሥልጠና አካሄደ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መስከረም 14 ቀን 2017 ዓ.ም. የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች አካታችነትን በተመለከተ ሥልጠና አካሄደ። ይኽን ሁሉም የቦርዱ ሥራ ክፍል ኃላፊዎችና ከፍተኛ ባለሞያዎች የተሣተፉበትን ሥልጠና በንግግር ያስጀመሩት የቦርድ አመራር አባሏ ብዙወርቅ ከተተ ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች አካታችነት ሲባል ተፈናቃዮቹ እንደ መራጭ ያላቸውን መብት በማረጋገጥ ሳንወሠን እነሱን ዕጩ ተመራጭ ሆነው ጭምር እንዲመጡ የሚያስችል ሥራ መሠራት ጭምር እንደሆነ ተናግረዋል። ይኽም ሲባል የተፈናቃዮቹን ተሣታፊነት ለማረጋገጥ በወጡ ድንጋጌዎች መሠረት መሥራት ብቻ ሣይሆን የተለያዩ መለኪያዎችን በማስቀመጥ የሕጎቹን ተፈጻሚነት ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። አክለውም ቦርዱ በቅርቡ ባስተዋወቀው የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅዱ ላይ “ራዕይ” እና “ቁልፍ ዕሴቶች” ብሎ ከዘረዘራቸው ውስጥ አካታችነት አንዱ እንደሆነና ለቦርዱ አካታችነት ትልቁ ትኩረቱ መሆኑን ተናግረዋል።
የቦርድ አመራሯን ንግግር ተከትሎ፤ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን አጠቃላይ ሁኔታ በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጉዳይ ባለሞያ በሆኑት አለምሸት ከበደ አማካኝነት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የተመለከተ አጠቃላይ መረጃ የሰጡ ሲሆን፤ የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ ፅንሰ-ሀሳቡንና እሱን የተመለከቱ ዓለም ዐቀፍና ሀገር ዐቀፍ የሕግ ማዕቀፎችን በተመለከተ ደ’ሞ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮ የሰብዓዊ መብቶች ባለሞያ በሆኑት ቴዎድሮስ ዳዊትና ኄኖክ ከበደ አማካኝነት ገለጻ ተሰጥቷል፤ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የምርጫ ተሣትፎና ያሉባቸው ውሥንነቶችን በተመለከተም እንዲሁ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባለሞያ በሆኑት ሔብሮን መስፍን አማካኝነት ማብራሪያ ተሰጥቷል።
በተጨማሪም የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የተመለከቱ የቦርዱ የሕግ ማዕቀፎችን በተመለከተ በቦርዱ የሕግ ሥራ ክፍል ኃላፊ አማካኝነት፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የምርጫ ተሣትፎ ላይ ያሉ ተሞክሮዎችን በተመለከተ ደ’ሞ የቦርዱ የኦፕሬሽን ሥራ ክፍል አስተባባሪ ባለሞያ አማካኝነት፤ እንዲሁም የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የምርጫ ተሣታፊነት ጥናት በተመለከተ ደግሞ በቦርዱ የሥርዓተ ፆታና አካታቸነት ሥራ ክፍል ከፍተኛ ባለሞያ አማካኘነት ቀርቧል።
የሥልጠናው ተሣታፊዎችን በተለያየ መልኩ ያሣተፈውን ሥልጠና በንግግር የዘጉት የቦርዱ ሰብሳቢ የሆኑት ሜላት ወርቅ ኃይሉ ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም ተፈናቃዮቹ ሁሉንም ዓይነት መብቶቻቸውን ለማግኘት ሁኔታዎች ውሥንነቶችን የሚፈጥሩባቸው በመሆኑ፤ እንደ ተቋም ከኛ የሚጠበቀው አንድም በምርጫ የሚኖራቸውን ተሣትፎ ማረጋገጥ ይሆናል ያሉት ሰብሳቢዋ፤ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን በምርጫ ማካተቱ፤ ተፈናቃዮቹ ካለባቸው የደኅንነት ሥጋትና ከመረጃ ውሥንነት አንጻር የግድ የሚል ተግባር እንደሆነ፤ እንዲሁም ምርጫውን የበለጠ ትርጉም የሚሰጡት እነኚኽን የማኅበረሰቡ ክፍሎች ማካተት ሲቻል ጭምር ነው ሲሉ አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።
በተጨማሪም ተፈናቃዮችን ተደራሽ የማድረግ ሥራው ሁኔታው ሲያጋጥም ሁኔታውን እየተከተሉ መልስ እየሰጡ መሄድ ብቻ ሣይሆን የዳበረ ፖሊሲዎችን አስቀድሞ በማውጣት ጭምር ሊሠራበት እንደሚገባው አሳስበዋል። በመጨረሻም ሥልጠናው ዕውን እንዲሆን ድጋፍ ላደረጉ አጋር ድርጅቶች፤ ሥልጠናውን ለሰጡ የውጭና የውስጥ ባለሞያዎች፤ እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲኽ የሚሰጣቸውን ሥልጠናዎች ተከታታይነት እንዲኖራቸው እያደረገና እያጠናከራቸው ለመጣው ለቦርዱ የሥርዓተ ፆታ እና አካታችነት ሥራ ክፍል ያላቸውን ከፍተኛ አድናቆት ገልጸዋል።