Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ጋር የምስጋና እና የልምድ ልውውጥ አካሄደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ጋር የምስጋና እና የልምድ ልውውጥ መድረክ አካሄደ። ቦርዱ በ6ኛው ሀገራዊ የቀሪና ድጋሚ ምርጫ በአፋር፣ በቤንሻንጉል-ጉሙዝ፣ በሶማሌ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ዜጎች ስለዴሞክራሲያዊ ምርጫ እና ሂደቶች ግንዛቤ እንዲጨብጡ የስነ ዜጋ እና መራጮች ትምህርት እንዲያገኙ ብሎም በተለያዩ የስነ ዜጋ ትምህርት እሳቤዋች ዙሪያ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የክርክር መድረኮች በማዘጋጀት በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት የክርክር ባህል እንዲጎለብት የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የሲቪል ማኅበራቱ የምስጋና እና የልምድ ልውውጥ አካሂዷል።

በቦርዱ የስነ ዜጋ እና መራጮች ትምህርት ክፍል አስተባባሪነት በተዘጋጀው የአንድ ቀን የምስጋና፣ የምክክር እና ልምድ ልውውጥ መድረክ 15 የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ለስነ ዜጋ እና መራጮች ትምህርት መጠናከር በተለያዩ የምርጫ ክልሎች ላበረከቱት የላቀ አስተዋፅኦ እንዲሁም ሌሎች ሰባት የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ደግሞ ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን እንዲያውቁ እና እንዲረዱ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ክርክሮችን ስላዘጋጁ የዕውቅና ሠርተፍኬት ተበርክቶላቸዋል።

በመድረኩ የመዝጊያ ስነ ስርዓት ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቦርድ አባል የሆኑት አቶ ፍቅሬ ገ/ሕይወት የሲቪል ማኅበራቱ እና የቦርዱ ሠራተኞች ለነበራቸው ቁርጠኝነት እና በዋጋ ለማይተመን አስተዋጾ አመስግነው የስነ ዜጋና የመራጮች ትምህርት አካታችነት እና ተደራሽነት አሁን ካለበት ደረጃ እንዲሻሻል የሲቪል ማኅበራት ጥረታቸው አጠናክረው እንዲቀጥሉ አደራ ብለዋል።

በምስጋና እና በምክክር መድረኩ የሲቪል ማኅበራቱ በ6ኛው ሀገር ዐቀፍ የቀሪና ድጋሚ ምርጫ የሥራ ሂደት የቀሰሙትን መልካም ተሞክሮዎችና ትምህርቶች፣ የገጠሟቸው ተግዳሮቶች፣ ለተግዳሮቶቹ የሰጡትን የመፍትሄ እርምጃዋች ብሎም የፓሊሲ እና የስትራቴጂ ምክረ ሃሳቦችን በመዘርዘር ለቀጣይ ሥራዎች በርካታ ጠቃሚ ግብዓቶች ተሰብስበዋል።

በዕለቱ የመድረኩ ታዳሚዎች በሥነ ዜጋ እና መራጮች ትምህርት ክፍል በተለያዩ ጊዜያቶች ተዘጋጅተው የቀረቡትን የማስተማሪያ እና መልዕክት ማስተላለፊያ በራሪ ፁሁፎች፣ አጫጭር የምስል እና የድምጽ መልዕክቶች፣ የማስተማሪያ መምሪያ እና ሌሎች የማስተማሪያ ቁሳቁሶች እንዲሻሻሉ እና ዘመኑን የዋጁ እንዲሆኑ ጥቅል የማሻሸያ መነሻ የግብዓት ሃሳቦች አቅርበዋል። በተለይ ሥራ ላይ ከዋለ አምስት ዓመታት ያለፈው የሥነ ዜጋ እና መራጮች ትምህርት ማስተማሪያ ማንዋል ከጭብጥ አግባብነት፣ ከተደራሽነት፣ ከአካታችነት እና ለአሰልጣኞችና ለተገልጋዮች ከሚሰጠው አመቺነት አንፃር የተገመገመ ሲሆን፣ በቀጣይ ሰፋ ባለ መርሃ ግብር ማንዋሉ እንደሚገመገም እና በሚመለከታቸው ባለሙያዋች እንደሚሻሻል ማወቅ ተችሏል።

Share this post