Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአካል ጉዳተኞች አካታችነት ላይ ሥልጠና አካሄደ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቦርዱ ሥራ ክፍል ኃላፊዎችና ከፍተኛ ባለሞያዎች የተሣተፉበትን ሥልጠና መርኅ-ግብር መስከረም 8 እና መስከረም 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሁለት ቀናት የአካል ጉዳተኞች አካታችነት ላይ ሥልጠና አካሄደ። ስልጠናዉን በንግግር ያስጀመሩት የቦርድ አመራር አባል የሆኑት ፍቅሬ ገ/ሕይወት ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም ቦርዱ በተለይም በምርጫ ወቅት ትኩረት ሠጥቶ ከሚሠራባቸው ጉዳዮች ውስጥ የአካል ጉዳተኞች አካታችነት ከዋነኞቹ እንደ አንዱ የሚጠቀስ መሆኑን፤ ይኽም ሥልጠና ቦርዱ ለጉዳዩ የሚሰጠው ትኩረት በምርጫ ወቅት ብቻ የተገደበ ላለመሆኑ ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል። አመራሩ፤ በተጨማሪም አካል ጉዳተኛ የማኅበረሰብ ክፍሎች በምርጫ ወቅት በበቂ ላለመሣተፋቸው ምን ዓይነት ተግዳሮቶች አሉባቸው የሚለውን በመለየት የመፍትሔውም አካል መሆን እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ሥልጠናው በዶ/ር ዮሐንስ ታከለ የተሰጠ ሲሆን፤ ዶ/ር ዮሐንስ ሥልጠናውን የሰጡት የተለያዩ ዓለም ዐቀፍ ፅንሰ-ሐሳቦችን፣ ትንተናዎችንና ሞዴሎችን እንዲሁም የሕይወት ተሞክሯቸውን ጭምር በማጋራት ነበር። በመድረኩ ሥልጠና ከመስጠት ባሻገር የተለያዩ ዓለም ዐቀፍ ሥምምነቶች እንዲሆም የምርጫ ዐዋጁ ላይ ያሉት ድንጋጌዎች ከአካታችነት አንጻር ያላቸው ፋይዳና ውሥንነቶች ላይ ሰፋ ያለ ውይይትና ክርክር የተደረገ ሲሆን፤ ድንጋጌዎቹን ገቢራዊ ከማድረግ አንጻር ያሉ ውሥንነቶችን በመለየት መፍትሔ ሊሆኑ የሚችሉ አማራጮች የትኞቹ ናቸው የሚለው ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጎባቸዋል።

ሁለት ቀን የፈጀውን የሥልጠና መርኅ-ግብር የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር የተጠናቀቀ ሲሆን፤ በንግግራቸውም ቦርዱ የአካል ጉዳተኛ አካታችነት ላይ በሰፊው ለመሥራት ያለው ፍላጎት ባለፉት የቦርዱ ምርጫዎች ላይ በግልጽ የታየ መሆኑን አስታውሰው፤ ነገር ግን የአካል ጉዳተኛ አካታችነትን ማረጋገጥ የሚቻለው በፍላጎት ብቻ ሣይሆን በዕውቀት ጭምር በመሆኑ ሥልጠናው ማስፈለጉን አስረድተዋል።

ተሣታፊ የሥራ ክፍል ኃላፊዎቹና ባለሞያዎቹ የአካል ጉዳተኞች አካታችነት የሚገለጽባቸው አንጻሮች ላይ፤ በተለይም በምርጫ ወቅት የአካል ጉዳተኛ አካታችነት ምን መምሰል አለበት የሚለው ላይ የተሻለ ግንዛቤ እንዳገኙ ዕምነታቸው እንደሆነ ገልጸው፤ ኃላፊዎቹ የወሰዱትን ሥልጠና በሥራ ክፍላቸው ላሉ ሌሎች ባለሞያዎችም የማጋራትና በሥራዎቻቸው ሁሉ ተፈጻሚ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በመጨረሻም ሥልጠናው ዕውን እንዲሆን የገንዘብ ድጋፍ ላደረገልን UNDP፤ ሥልጠናውን ለሰጠው ባለሙያ ዶ/ር ዮሐንስ እና ሥልጠናውን ላዘጋጀውና ላስተባበረው የቦርዱ ሥርዓተ ፆታና አካታችነት ሥራ ክፍል እንዲሁም አስተዋፅዖ ላደረጉ ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበው ሥልጠናው ተጠኗቋል።

Share this post