የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቀጠናዊ የምርጫ ሥጋት አስተዳደር ልምድ ልውውጥ አውደ ጥናት ላይ ተሣተፈ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዲስ አበባ በተካሄደው በቀጠናዊ የምርጫ ሥጋት አስተዳደር ልምድ ልውውጥ ላይ ተሣተፈ። ነሐሴ 20 እና 21 ቀን 2016 ዓ.ም. በተካሄደው ቀጠናዊ ልምድ ልውውጥ አውደ ጥናት ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአራት ሀገራት ማለትም ከኬንያ፣ ቦትስዋና፣ ማላዊና ሴራሊዮን የመጡ የምርጫ ቦርድ አመራሮችና ባለሞያዎች የተሣተፉ ሲሆን፤ የልምድ ልውውጥ መድረኩም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ተጀምሯል። ሰብሳቢዋ በመክፈቻ ንግግራቸው ይኽ ቀጠናዊ የሥጋት አስተዳደር የልምድ ልውውጥና ሥልጠና ሀገራቱ በምርጫ ጉዳይ ላይ ያላቸውን ዕውቀት፤ልምድ እንዲለዋወጡና አንዳቸው ከሌላቸው የተሻለ ተሞክሯቸውን እንዲወስዱ የሚያስችል መሆኑን፤ ይኽም እርስ በርስ በመደጋገፍ በጋራ ለማደግ እንደሚያስችል ገልጸዋል።
የሥጋት አስተዳደር ልምድን የተሻለ ተሞክሮ ካላቸው ሀገራት በመውሰድ በሀገር ውስጥ ማዳበር ቅንጦት ሣይሆን ሁሉም ምርጫ ቦርዶች ሊተገብሩት የግድ የሚል መሆኑን የገለጹት ሰብሳቢዋ፤ ይኽውም በዕጩዎች፣ በመራጮችና በታዛቢዎች፣ እንዲሁም ለቦርዱ ሠራተኞች በሚሰጡ የተለያዩ የሥራ ሥምሪትና አፈጻጸሞች ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ዕክሎችን ለማስቀረት ካልተቻለም በቀላሉ መቆጣጠር በሚቻሉበት ደረጃ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ገልጸዋል። በመጨረሻም ይኽን የልምድ ልውውጥ እንዲሳካ አስተዋፅዖ ያደረጉ አካላትን አመስግነዋል።
የልምድ ልውውጡን ዋና ዐላማና አጠቃላይ ይዘት በተመለከተ የምርጫ ግጭትና ሥጋት አስተዳደር ዘርፍ አማካሪ በሆኑት ሴዐድ አሊሆድዚች አማካኝነት ገለጻ የተሰጠ ሲሆን፤ ገለጻውን ተከትሎም ከኬንያ በመጡት የሥጋትና የምርጫ ደኅንነት ባለሞያ በሆኑት ሊኖስ ኦንያንጎ አማካኝነት የምርጫ አስፈፃሚ አካላትን ስለሚያጋጥሟቸው ነባራዊና አውዳዊ የምርጫ ሥጋት አስተዳደር አመላካች ሁነቶች በዝርዝር ቀርበዋል።
የምርጫ አስፈፃሚ አካላት ሥጋትን ማስተዳደር የሚያስችላቸውን ማዕቀፎች እንዴት ማዳበር ይቻላል የሚለውንና ስጋቱንም ለመመከት ሊከተሏቸው የሚገቡ የመፍትሔ መሣሪያዎችን በተመለከተ የምርጫ ግጭትና ሥጋት አስተዳደር ዘርፍ አማካሪ በሆኑት ሴዐድ አሊሆድዚች እና ከኬኒያ በመጡት ሊኖስ ኦንያንጎ አማካኝነት ገለፃ ተደርጓል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከቦትስዋና በመጡት የቦትስዋና ምርጫ ቦርድ የዐቅም ማጎልበት አስተባባሪ በሆኑት ባፈለጥሴ ቡታሌ እንዲሁም ከሴራሊዮን በመጡት የሴራሊዮን ምርጫ ቦርድ የቦርድ አመራር አባሏ ዛይናብ ኡሙ ሞሰራይ አማካኝነትም በጉዳዩ ላይ በየተራ ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቷል።
በልምድ ልውውጥ መድረኩ ወቅት በሁሉም አጀንዳዎች ላይ የየዘርፉ ባለሞያዎች ማብራሪያ እንዲሰጡበት እየተደረገ የሁሉም ሀገራት ተሣታፊዎች በቡድን በቡድን እየተወያዩ የየሀገራቸውን ተሞክሮ እንዲያቀርቡ ተደርጓል።
በልምድ ልውውጡ ላይ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ ከቦርዱ አመራርና ከቦርዱ የተለያዩ የሥራ ክፍሎች የተውጣጡ ባለሞያዎች እንዲሣተፉ ተደርገዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደ አዲስ ከተቋቋመ ጊዜ አንሥቶ በስፋት ከሠራቸው ሥራዎች ውስጥ ራሱን በብቁ ባለሞያዎች ማደራጀትና ምርጫና ከምርጫ ጋር የተያያዙ ሥልጠናዎችን የቦርዱ ባለሞያዎች እንዲወስዱ ማስቻል መሆኑ ይጠቀሳል።