የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተማሪዎች የክርክር መድረክ በአዳማ ከተማ አካሔደ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የስነ-ዜጋና መራጮች ትምህርት ሥራ ክፍል ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል አንዱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በዲሞክራሲያዊ ምርጫ እና የዜጎች ተሳትፎ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን ማዘጋጀት ዋነኛዉ ነዉ፡፡ በመሆኑም ቦርዱ ከላባ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ጋር በመተባበር፣ በአዳማ ከተማ ናፊያድ ት/ቤት በተግባር የተደገፈና ለተማሪዎች ግንዛቤን የሚያስጨብጥ የክርክር እና የምርጫ ናሙና ኹነት አካሒዷል፡፡ በመድረኩ የትምህርት ቤቱ አስተዳደር አካላትን ጨምሮ ወላጆች፣ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ አካል ጉዳተኞች፣ ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የተዉጣጡ ጋዜጠኞች እና ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡
የክርክሩ ዋና ፍሬ ሀሳብም ‘የአመራርነትን ሚና ሴቶች ወይስ ወንዶች ቢወስዱ የተሻለ ነዉ?’ በሚል ርዕሰ-ጉዳይ ዙሪያ ሲሆን ተከራካሪዎቹ በቀረቡት ርዕሶች ላይ ተሟግተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ተማሪዎች ከወዲሁ የምርጫ ሂደትን አንዲለማመዱ ይረዳቸዉ ዘንድ በመድረኩ ታዛቢዎች እና አስመራጭ ኮሚቴዎች በተገኙበት ተማሪዎቹ የየራሳቸዉን የፖለቲካ ምስለ-ፓርቲ በማዋቀር የናሙና ምርጫ አካሒደዋል፡፡
የምርጫ ሂደት ልምምዱ፤ አስመራጭ ኮሚቴ፣ ሁለት ናሙና የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ታዛቢዎች፣ የድምፅ መስጫ ቦታ፣ የድምፅ መስጫ ናሙና ካርድና የድምፅ መስጫ ሳጥን የተዘጋጀለት ሲሆን፤ ተማሪዎቹ ያዋቀሩትን የፖለቲካ ምስለ-ፓርቲ በመወከል በተሰጣቸው የመከራከሪያ ሀሳብ ላይ ሰፊ ክርክር አካሒደዋል፡፡ የትምህርት ቤቱ ርዕሰ-መምህር በበኩላቸዉ ሂደቱ ተማሪዎች ስለዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሂደት ግንዛቤ ያገኙበት እና በተግባር የተደገፈ ልምምድ እንዲያደርጉ እድሉን ያመቻቸላቸዉ መድረክ ነዉ ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም የላባ ሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ ይህ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አንዲዘጋጅ ከፍተኛ ድጋፍ ያደረገዉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን በማመስገን መድረኩ ተማሪዎች በአመክንዮ እና ምክንያታዊነት ላይ የተመሰረተ የክርክር ባህልን እንዲያዳብሩ የሚያስችል እና የዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሂደትን በተግባር ልምምድ እንዲያደርጉ እገዛ ያደረገ በመሆኑ ቦርዱ ይህን መሰል መድረክ ማዘጋጀቱን ለወደፊትም አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡