የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ሥጋት አስተዳደርና የምርጫን ተዓማኒነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ማዕቀፍን የተመለከተ ዐውደ ጥናት አካሄደ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ትላንት ሐምሌ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. የሥጋት አስተዳደርና የምርጫን ተዓማኒነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ማዕቀፍን የተመለከተ ዐውደ ጥናት አካሄደ። በዐውደ ጥናቱ ላይ የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላት ወርቅ ኃይሉን ጨምሮ አምስቱም የቦርድ አመራር አባላት የተገኙ ሲሆን፤ የቦርዱ የየሥራ ክፍል ኃላፊዎችም ተገኝተዋል። ዐውደ ጥናቱን የቦርድ አመራር አባሏ ብዙወርቅ ከተተ በንግግር የከፈቱት ሲሆን፤ በንግግራቸውም ዐውደ ጥናቱ በዋናነት ዓላማው ያደረገው ቦርዱ ከሣምንታት በፊት ያስተዋወቀውንና ቦርዱ እንደአዲስ ከተቋቋመ ወዲህ መጀመሪያ የሆነውን የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድን በመተግበር ሂደት የተለያዩ ተግዳሮቶች ቢገጥሙት እንዴት ባለ’አግባብ ሣይንሳዊ መንገድን ተከትለን መፍታት እንችላለን፤ በዚህም ሂደት ማን ምን ሚና አለው የሚለውን መገምገምና መለየት በማስፈለጉ እንደሆነ አብራርተዋል።
በዐውደ ጥናቱ ላይ የምርጫ ሥጋት አስተዳደር መገለጫ ባህሪያትን አስመልክቶ በ International IDEA- Regional Thematic Lead on Electoral Processes ላይ ባለሞያ በሆኑት ኦሉፉንቶ አኪንዱሮ አማካኝነት ገለጻ ተደርጎ ውይይት የተደረገ ሲሆን፤ የምርጫ ሥጋት አስተዳደርን አስመልክቶ ራስን የመገምገሚያ ሥነ -ዘዴና መለኪያዎቹን አስመልክቶ ደግሞ በ International IDEA- Elections Programme Officer ባለሞያ በሆኑት ቬራ ሙሪንግ አማካኝነት ማብራሪያ ተሰጥቷል። ይኽንንም ተከትሎ ሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ፤ ማለትም፤ በኢትዮጵያ የምርጫን ተዓማኒነትን ለማረጋገጥ ተግዳሮት የሆኑት የትኞቹ ጉዳዮች ናቸው፤ ለተግዳሮቶቹ መፍትሔ ለማስገኘትስ ለቦርዱ በሕግ የተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት ምን ያኽል ጠቅሟል፣ የምርጫ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የትኞቹ የሕግና ተቋማዊ ደኅንነት መጠበቂያዎችን መጠቀም ይቻላል፣ እንዲሁም የትኞቹ አስተዳደራዊ ሥርዓቶች የምርጫ ተዓማኒነትን በተለየ ለመጠበቅ ይረዳሉ የሚሉት ላይ አመራሮቹ በቡድን በቡድን ሆነው ግምገማዎችን ያደረጉ ሲሆን፤ በመጨረሻም የየቡድኑ ተወካዮች የየቡድናቸውን ግኝቶች በዝርዝር አቅርበዋል።
ዐውደ ጥናቱ የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር የተጠናቀቀ ሲሆን፤ በንግግራቸውም ዐውደ ጥናቱ ጊዜውን የጠበቀ መሆኑን፤ ይኽም ሲባል የምርጫ ሥጋት አስተደደርን የተመለከተው ግምገማ ቦርዱ በቀጣይ ለሚያከናውናቸው የአካባቢያዊ ምርጫም ሆነ ሀገራዊ ምርጫ ጉልኅ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል። እያንዳንዱ የሥራ ክፍል በተናጠልና እንደ ተቋም የተለያዩ ተግዳሮቶችን ቢቻል ለማስቀረት ካልሆነም የጉዳት መጠናቸውን ለመቀነስ ሲከተለው የመጣውን የሥጋት ማስተዳደር ሥነ-ዘዴን እንዲኽ ባለ መልኩ በጋራ መገምገሙ እጅግ ጠቃሚ በመሆኑ፤ ዐውደ ጥናቱ ፋይዳው ብዙ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተው አብራርተዋል። ቦርዱ ሲያከናውናቸው የቆየውን እጅግ ተስፋ ሰጪ አፈጻጸሞች የተለያዩ ተግዳሮቶች አፈጻጸሙን ባስገኘው ውጤት ልክ እንዳይመዘን ያደረጉበት አጋጣሚዎች እንደነበሩና፤ ይኽ ዐውደ ጥናት መሰል ተግዳሮቶችን ለመለየት እንደሚረዳና የቦርዱን የቅድመ ሥጋት ትንተና የማድረግ ዐቅም እንደሚጨምር እምነታቸው እንደሆነ ተናግረዋል። በመጨረሻም ለዐውደ ጥናቱ ቴክኒካል ድጋፍ ላደረጉ ባለድርሻ አአካላት ምስጋናቸውን ገልጸዋል።