የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሴፍ ላይት ኢኒሼቲቭ ጋር በመተባበር የወጣቶች የክርከር መድረክ አዘጋጀ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫ ሂደት እና በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ዙሪያ የወጣቶች ተሳትፎን ለማጉላት ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ሰኔ 1 እና 8 ቀን 2016 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል በቢሾፍቱ እና ጅማ ከተሞች ቦርዱ ሴፍ ላይት ኢኒሼቲቭ ከተባለ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ጋር በመተባበር ወጣቶች የተሳተፉበትን የክርክር መድረክ አካሔዷል፡፡ የክርክር መድረኩ መክፈቻ ፕሮግራም ሰኔ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ በርታ ደበሌ ሆቴል የተካሄደ ሲሆን ቀጣይ መድረኩ ሰኔ 8 ቀን 2016 ዓ.ም. ጅማ ከተማ አሜሪካን ኮርነር የህዝብ ላይብረሪ ዉስጥ ተካሔዷል፡፡
የክርክሮቹ ዋና ፍሬ ሀሳቦች በሶስት ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ሲሆን እነዚህም ‘በምርጫ ወቅት ድምፅ መስጠትን አስገዳጅ ማድረግ የመራጮች ተሳትፎን በመጨመር በኢትዮጵያ ዴሞክራሲን ያጠናክራል ወይ?’ ‘ሰላማዊ እና ስኬታማ ምርጫን ለማካሔድ ከማህበራዊ እና ከዋና (ሜይንስትሪም) ሚዲያዎች አዎንታዊ ሚና ያለዉ የትኛዉ ነዉ?’ እንዲሁም ‘የስርዓተ-ጾታ እኩልነት ማበረታቻ ትግበራ አፈርማቲቭ አክሽን የሴቶች ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎን በማሳደግ ረገድ አስተዋፆ አለው ወይ?’ በሚሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡
በሁለቱም ከተሞች በተካሔዱት ዝግጅቶች ከማህበረሰቡ የተዉጣጡ ወጣቶች፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እና አካል ጉዳተኞች በክርክሩ ላይ ተሳትፈዋል፡፡ እንዲሁም የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት ተወካዮች፣ የወጣቶች እና ስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ እና የአከባቢዉ ወጣቶች መርሀግብሩን ታድመዋል፡፡ የሴፍ ላይት ኢኒሼቲቭ መስራች እና ሥራ አስኪያጅ ይህን መሰል መድረኮች ወጣቶች ገዢ እና ምክንያታዊ ሀሳቦችን በጠረጴዛ ዙሪያ በመሞገት የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደትን የሚለማመዱበት እድል ያመቻቻል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የስነ-ዜጋና መራጮች ትምህርት ሥራ ክፍልን በመወከል በሁለቱም መድረኮች የተገኙ ባለሙያዎች በበኩላቸዉ ወጣቶች በሀገሪቱ አብዛኛዉን የህዝብ ቁጥር እንደመወከላቸዉ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ላይ የሚኖራቸዉ ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስ ለወደፊትም ይህን መሰል የወጣቶች አካታች መድረኮች ተጠናክረዉ እንደሚቀጥሉ አስታዉቀዋል፡፡