የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በወላይታ ሶዶ እና አርባምንጭ ከተሞች የክርክር መድረክ አካሔደ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እና የምርጫ ሂደቶች ዙሪያ ዜጎችን ለመድረስ ያስችለዉ ዘንድ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ቦርዱ ድሪም ፎር ዴቨሎፕመንት ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ከተባለ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ጋር በመተባበር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፡ ወላይታ እና አርባ ምንጭ ከተሞች በተማሪዎች፣ አካል ጉዳተኞች እና ሴቶች መካከል ሶስት የክርክር መድረክ አካሂዷል፡፡ የክርክሩ ጭብጡም በሶስት ርዕሰ-ጉዳዮች ዙሪያ ላይ ያተኮረ ሲሆን እነርሱም፡ ለሀገር ህልዉና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ግዴታ ነዉ ወይስ አይደለም?፣ማህበረሰቡ ስለ አካል ጉዳተኞች ያለዉ የተዛባ አስተሳሰብ አካል ጉዳተኞች በምርጫ ዙሪያ እኩል ተሳትፎ እንዳይኖራቸዉ አድርጓል ወይስ አላደረገም?፣ ሴቶች በምርጫ ወቅት በመምረጥ ነው ወይስ በመመረጥ የተሻለ ተሳትፎ የሚኖራቸዉ? በሚሉ የመከራከሪያ ሀሳቦች ዙሪያ ነዉ፡፡
በክርክር መድረኩ ላይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የስነ-ዜጋ እና መራጮች ትምህርት ባለሙያን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣አካል ጉዳተኞች፣ሴቶች፣ከአከባቢዉ ማህበረሰብ የተዉጣጡ ወጣቶች እና ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡ በእለቱ ንግግር ያደረጉት የድሪም ፎር ዴቨሎፕመንት ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሳሁን አሰፋ በበኩላቸዉ ይህን መሰል አካታች ፕሮግራሞች መካሔዳቸዉ ዜጎች በሀገራቸዉ ጉዳይ ላይ እኩል የመሳተፍ መብት እንዳላቸዉ ማሳያ መሆን የሚችል መድረክ ነዉ ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የስነ-ዜጋ እና መራጮች ትምህርት ሥራ ክፍልን በመወከል በመድረኩ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ባለሙያዎች በበኩላቸዉ ቦርዱ ሁሉም ዜጎች ሀገራዊ ጉዳይ ላይ እኩል ተሳትፎ ያላቸዉ ቢሆንም በማህበረሰቡ ዉስጥ ባሉ የተዛቡ አመለካከቶች እና ባህላዊ ተፅእኖዎች ምክንያት የእኩል ተሳታፊነት እድልን ማግኘት ያልቻሉ እንደ ሴቶች እና አካል ጉዳተኞች ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለመድረስ ቦርዱ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ እና ይህን መሰል መድረኮችም ተጠናክረዉ እንደሚቀጥሉ አስታዉቀዋል፡፡