የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተማሪዎች የክርክር መድረክ በድሬደዋ ከተማ አካሔደ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሕግ ከተሰጡት ኃላፊነቶች መካከል ዜጎች ስለ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሂደቶች በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸዉ ማስቻል አንደኛዉ ነዉ፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የስነ-ዜጋ እና መራጮች ትምህርት ሥራ ክፍል ከሐበጋር ዲቤትስ (ደበበ ኃ/ገብርኤል ከተባለ የሕግ ቢሮ) ጋር በመተባበር ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች በተወከሉ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መሀከል የክርክር መድረክ በድሬደዋ ከተማ አካሄዷል፡፡ የክርክሩ ጭብጥም በሁለት ርዕሰ-ጉዳዮች ዙሪያ ላይ ያተኮረ ሲሆን፡ ለኢትዮጵያ የሚሻለዉ የመንግስት ሥርዓት ፌደራላዊ ወይስ አሃዳዊ? እና ዴሞክራሲ ተመራጭ የፖለቲካ ሥርዓት ነዉ ወይስ አይደለም? በሚሉ ሀሳቦች ዙሪያ ነዉ፡፡
ተማሪዎቹ በሁለቱም ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ከዳኞች እና ታዳሚዎች በሚነሱላቸዉ ጥያቄዎች መሰረት ጥልቅ ክርክር ያደረጉ ሲሆን፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የድሬደዋ አስተዳደር ቅ/ጽ/ቤት የስነ-ዜጋ እና መራጮች ትምህርት ባለሙያዎችን ጨምሮ የከተማዉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች፣ተማሪዎች እና ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች በፕሮግራሙ ላይ ተሳትፈዋል፡፡
ከክርክሩ መርኃ-ግብር በኋላም ተማሪዎች የምርጫ ሂደትን ከወዲሁ እንዲለማመዱ ለማስቻል ይረዳ ዘንድ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት የተካሔደ ሲሆን በመራጮች አብላጫ ድምፅ ያገኘዉ የመከራከሪያ ሀሳብም አሸናፊ ሆኗል፡፡
በመጨረሻም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን በመወከል በፕሮግራሙ ላይ ንግግር ያደረጉ ባለሙያዎች በበኩላቸዉ ይህ አይነቱ የሀሳብ ሙግት ወጣቶች በውይይት እና በዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ የዳበረ ማንነት እንዲያጎለብቱ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለዉ እና የመጀመሪያ መራጭ የምንላቸዉን የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረዉ በመግለፅ ተመሳሳይ መድረኮችም ለወደፊቱ እንደሚቀጥሉ አስታዉቀዋል፡፡