የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተለያዩ የወጣቶች የክርክር መድረክን አዘጋጀ
የኢትዯጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ኮሚኒቲ ሰስተነብል ዴቬሎፕመንት ኤይድ ከተባለ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ጋር በመተባበር በ 3 የተለያዩ ከተሞች ማለትም ወላይታ ሶዶ፥ ሆሳዕና እና ወልቂጤ የክርክር መድረክ አካሂዷል። ይህ የክርክር መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ፥ በሆሳዕና ከተማ ዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም በወልቂጤ ከተማ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የተካሄደ ሲሆን የሕግ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እና የዩኒቨርሲቲዎቹ ማህበረሰብ አባላት ተሳትፈዋል። ክርክሩም በዋናነት በምርጫ ፥ዲሞክራሲና በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ ሲሆን ተማሪዎች በንድፈ-ኃሳብ ደረጃ የተማሯቸውን ፅንሰ-ሀሳቦች ተግባራዊ እንዲያደርጉ እድል ያመቻቸ መድረክ መሆኑ ተጠቅሷል።
በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው የክርክር መድረክ ‘በኢትዮጵያ ፓርላሜንታዊ ወይስ ፕሬዜዳንታዊ የመንግስት ስርዓት የተሻለ ነው?’ በሚል ርዕሰ-ጉዳይ ተማሪዎች ክርክር ያደረጉ ሲሆን በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዜዳንት በበኩላቸው ክርክር የሚደረግባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ወቅታዊና ወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች በመሆናቸው በሀገራችን በሚካሄዱ የዲሞክራሲ ግንባታ ሂደቶች ላይ ከፍተኛ አስተዋጾ ይኖራቸዋል ብለዋል።
የክርክር መድረኩ ሶስተኛ ዙር በዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ የተካሄደ ሲሆን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ምርምር ፥ ቴክኖሎጂ ሽግግርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዜዳንት ይህን መድረክ ያዘጋጁትን አካላት በማመስገን እንዲህ አይነቱ ዝግጅት ተማሪዎች ነገ ተመርቀው ወደ ማህበረሰቡ ሲቀላቀሉ በምን መልኩ የማህበረሰቡን ችግር መቅረፍ እንደሚገባቸው ልምድ የሚቀስሙበት የልምምድ መድረክ እንደሆነ ጠቁመዋል። በተጨማሪም ምክትል ፕሬዜዳንቱ ተማሪዎች የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልዶች እንደመሆናቸው መጠን በእንደዚህ አይነት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በመወያየት እና በመከራከር ከወዲሁ ልምምድ ማድረጋቸው ነገ ወደ ሥራ አለም ሲቀላቀሉ ሀገሪቱ በዘርፉ የምትፈልገውን ለውጥ ለማምጣት እገዛ እንደሚያደርግላቸው አስገንዝበዋል።
በመጨረሻም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የስነ-ዜጋና መራጮች ትምህርት ሥራ ክፍል ከኮሚኒቲ ሰስተነብል ዴቬሎፕመንት ኤይድ ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን የክርክር መድረክ ሲያጠናቅቅ ክርክሩ ወጣት ተማሪዎች በዲሞክራሲና የዜጎች ተሳትፎ ዙሪያ በንድፈ-ኃሳብ ደረጃ የቀሰሙትን እውቀት በተግባር የፈተሹበት መድረክ መሆኑንና የታለመለትን ግብ ማሳካቱን በመገንዘብ ለዝግጅቱ ስኬት አስተዋጽኦ ያደረጉትን አካላት በሙሉ አመስግኗል።