ቦርዱ የ6ኛውን ሀገር አቀፍ ቀሪና የድጋሚ ምርጫ ውጤት ይፋ አድርጓል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቤንሻንጉል-ጉሙዝ፣ በአፋር፣ በሶማሌ እና በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ያካሄደውን የ6ኛው ዙር ሀገር አቀፍ ቀሪና የድጋሚ ምርጫ ውጤት ሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል።
የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ በተጠቀሱት አራቱ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 29 ምርጫ ክልሎች ስር በሚገኙ በ1218 ምርጫ ጣቢያዎች መካሄዱ የታወቀ ሲሆን ውጤት ይፋ በማድረጊያ መርኃ-ግብሩ ላይ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች (ተወካዮች)፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያቀረቡአቸው ዕጩዎች፣ የግል ዕጩ ተወዳዳሪዎች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኃላፊዎችና ተወካዮች፣ የሚዲያ አካላት፣ የፌዴራልና የክልል የጸጥታ አካላት እና ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች ታዳሚ ነበሩ።
"እንደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰላማዊ፣ ነፃ እና ገለልተኛ ምርጫ ለማካሄድ ጥሩ ዝግጅት አድርገን፣ በአንፃራዊ ደረጃ የ6ኛውን ዙር ሀገራዊ ቀሪና ድጋሚ ምርጫ በስኬት አከናውነናል። ሁላችሁም ለነበራችሁ ንቁ ተሳትፎ እና ትጋት ከልብ አመሠግናለሁ።" ያሉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ኃይሉ የምርጫውን ውጤት በፀጋ መቀበል በአራቱም ክልሎች ወጥቶ የመረጠውን የመራጭ ድምፅ ማክበር ነው ብለዋል።
በዚህ የ6ኛው ዙር ቀሪና የድጋሚ ምርጫ ከምርጫ አስፈፃሚዎች፣ ከክልል የምርጫ ሠራተኞች ባሻገር ከቦርዱ ሠራተኞች የተውጣጡ 29 የቁጥጥርና ክትትል ቡድንን በማደራጀት በየምርጫ ጣቢያዎች ልከን ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርጉ በማድረጋችን ጉልህ ችግር ሳይከሰት ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን አስችሏል ያሉት ወ/ሮ ሜላትወርቅ ምርጫው እንዲሳካ ቀን ከሌት ለተጉ ባለድርሻ አካላት፣ የቦርዱ አመራር አባላትና ሠራተኞች ምስጋናቸውን እና አድናቆታቸውን ገልፀዋል።
ቦርዱ ሰኔ 27 ቀን 2016 ዓ.ም የምርጫ ውጤት ይፋ ለማድረግ ዕቅድ የያዘ ቢሆንም ለሁለት ቀናት የዘገየው እና ዛሬ ሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ይፋ የተደረገው በ140 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የቀረቡ የምርጫ ሂደት አቤቱታዎችን በመመርመር ውሳኔ ለመስጠት አስፈላጊ ስለነበረ ነው ያሉት የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ ቦርዱ በዚህ ምርጫ ለተሳተፉ 12 የፖለቲካ ፓርቲዎች አጠቃላይ 21 ሚሊዮን ብር የምርጫ በጀት፣ በግል ለቀረቡ 12 ዕጩዎች ደግሞ ለእያንዳንዳቸው የ100 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል። በመርኃ ግብሩ ላይ የታደሙት ከኅብረት ምርጫ (CECOE) የምርጫ ታዛቢዎች ተወካይ በአራቱም ክልሎች ምርጫው ከነበሩበት ውስን ክፍተቶች በስተቀር ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ነበር ያሉ ሲሆን የምርጫ አስፈፃሚዎች ተወካይ ወ/ት ሊያ አገሬ በበኩላቸው ምርጫን ማስፈፀም ሥራ ብቻ ሳይሆን እንደ ዜጋ ምርጫው ተዓማኒ እና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን በዚህ የቀሪና ድጋሚ ምርጫ ከልብ ደክመናል፣ የምርጫ አፈፃፀም ክህሎታችንንም ከጊዜ ወደጊዜ ጎልብቷል ብለዋል።
በቤንሻንጉል-ጉሙዝ በልዩ ሺናሻ ምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ተወዳድረው ያሸነፉት የቦሮ ዲሞክራሲ ፓርቲ አመራር ዶ/ር መብራቱ አለሙ ምርጫው በተዓማኒነትና በገለልተኝነት ተከናውኖ መጠናቀቁን ገልፀው፣ ከሁለት ዓመት በኃላ ለሚካሄደው ሀገራዊው 7ኛው ዙር ምርጫ ይህ የምርጫ ሂደት እና የቀሰምናቸው ልምዶች ያግዛሉ ብለዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘም የጉሙዝ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር እና በያሶ የምርጫ ክልል ለክልል ምክር ቤት አሸናፊ የሆኑት አቶ ግራኝ ጉደታ በበኩላቸው ምርጫው በሰላም ተጀምሮ በሰላም በመጠናቀቁ ደስተኞች ነን።" ብለዋል።
ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. በተካሄደው የ6ኛው ዙር ሀገራዊ ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫ በተለያዩ ምክንያቶች ከምርጫ ወይም ከውጤት ውጭ የተደረጉ ምርጫ ጣቢያዎችን ሳይጨምር በአጠቃላይ ከተመዘገቡ 901,352 መራጮች መካከል 766,198 ዜጎች ድምፃቸውን በመስጠታቸው የምርጫ ቀን የድምፅ መስጠት ተሣትፎ (voter turnout) 85 በመቶ መሆኑ ታውቋል።