የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሴንተር ፎር ኢምፓዎርመንት ኢትዯጵያ አሶሲዬሽን ከተባለ የሲቪል ማህበር ድርጅት ጋር በመተባበር የክርክር መድረክ አካሄደ
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የስነ-ዜጋና መራጮች ትምህርት የሥራ ክፍል የተለያዩ ሲቪል ማህበራት ድርጅቶችን በማቀናጀት እና የተመረጡ ውጤታማ ዘዴዎችን በመጠቀም በምርጫ ዲሞክራሲያዊ ሂደት ፥ የዜጎች ተሳትፎና ተያያዥ ርዕሰ-ጉዳዮች ዙሪያ ት/ት እየሰጠ ይገኛል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሴንተር ፎር ኢምፓዎርመንት ኢትዯጵያ አሶሲዬሽን ከተባለ የሲቪል ማህበር ድርጅት ጋር በመተባበር ከግንቦት 24/2016 ጀምሮ በሦስት ዙር የተከፋፈለ የክርክር መድረክ በወላይታ ሶዶ፥ ወራቤ እና ዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ተማሪዎችን በማሳተፍ አካሂዷል።
በግንቦት 27 2016 ወራቤ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው የክርክር መድረክ የዩኒቨርሲቲው የህግ ት/ቤት ተማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፥ የኮሌጅ ዲኖች፥ መምህራንና ተማሪዎችም ክርክሩን ታድመዋል። የክርክሩ ዋና ጭብጥ በምርጫና ዲሞክራሲ ዙሪያ ሲሆን በመድረኩ ላይ ሲንፀባረቁ ከነበሩት የክርክር ርዕሰ ጉዳዮች መካከል አንዱ ‘በሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር በህግ ቢገደብ ይሻላል ወይስ ባይገደብ’ የሚል ነበር። ይህንን የክርክር መድክረክ ያስጀመሩት የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ የነገ ሀገር ተረካቢ ተማሪዎቻችን እንዲህ አይነት አንገብጋቢ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ መሳተፋቸው ወደፊት የለውጥ ሞጋች እንዲሆኑና የተሻለች ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደት ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል ሲሉ በአጽንኦት አስገንዝበዋል። በተመሳሳይ መልኩ በግንቦት 28 2016 በዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው የክርክር መድረክ የስርዓተ ፆታ አካታችነትን የተመለከተ ክርክር በ4ኛ እና 5ኛ አመት የህግ ት/ቤት ተማሪዎች መካከል የተካሄደ ሲሆን ከፍተኛ የዩኒቨርሲቲው የሥራ አመራሮችን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የመድረኩ ታዳሚ ነበር።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሴንተር ፎር ኢምፓዎርመንት ኢትዯጵያ አሶሲዬሽን ጋር ያዘጋጀው ይህ የክርክር መድረክ ተማሪዎች ስለዲሞክራሲያዊ ምርጨዓ ያላቸውን ግንዛቤ የሚያሳድግ በመሆኑ መሰል ፕሮግራሞች ለወደፊት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጧል።