የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ‘ውመን ኢን ማይስ ኢትዮጵያ’ ከተባለ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ጋር በመተባበር በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሂደት እና የሴቶች ተሳትፎ ላይ ያተኮረ የክርክር መድረክ በወላይታ ዞን የተለያዩ ከተሞች አካሄደ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሕግ ከተሰጡት ኃላፊነቶች መካከል አንዱ ዜጎች በእውቀት ላይ የተመሰረተ ምርጫ እንዲደርጉ የስነ- ዜጋና መራጮች ትምህርትን ማዳረስ ነው። በመሆኑም ቦርዱ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የመራጮች መረጃ እና ትምህርትን ወደ ማህበረሰቡ ለማድረስ ከተለያዩ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በጋራ እየሠራ ይገኛል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ግንቦት 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ የቦርዱ የስነ-ዜጋና መራጮች ትምህርት የሥራ ክፍል ከ’ውመን ኢን ማይስ ኢትዮጵያ’ ጋር በመተባበር አራት የክርክር መድረኮች በወላይታ ዞን ሶስት ከተሞች ያካሄደ ሲሆን በክርክሩም የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን ጨምሮ ሌሎች ወጣት ሴቶች ተሳታፊ ሆነዋል። ክርክሩ በቅድሚያ በኪንዶ ኮይሻ ወረዳ በበሌ አዋሳ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች እና ተማሪዎች መካከል የተካሄደ ሲሆን የክርክሩ ጭብጥ በሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ፣ ተጠቃሚነት እንዲሁም አሉታዊ ጫና በሚያሳርፉ እሳቤዎች ላይ ያተኮረ ነበር። የክርክር መድረኩ በቀጣዩ ቀን በቦሎሶ ቦምቤ ወረዳ ቀጥሎ የዋለ ሲሆን የ ‘ውመን ኢን ማይስ ኢትዮጵያ’ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ አባይነሽ አሽኮ ይህ ውይይትና የክርክር መድረክ ሴቶችን ለማብቃት በሚደረገው ጥረት የተሻለ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ መሆኑን ገልጸዋል። ሶስተኛው የሴቶችና ወጣቶች የክርክርና የውይይት መድረክ በኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ ተካሂዷል። የወረዳው ዋና አስተዳደሪን ጨምሮ የተለያዩ የወረዳው የመንግስት ሥራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን የወጣቶችን ተሳትፎ በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታና ሌሎች ዘርፎች ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካለት ሊደግፉ ይገባል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም የውድድሩ የማጠቃለያ መድረክ ግንቦት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. በወላይታ ሶዶ ከተማ በጉተራ የሥልጠና ማእከል ሞቶሎሚ አዳራሽ የተካሄደ ሲሆን የወላይታ ዞን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ፥ ተወዳዳሪዎች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በማጠቃለያ ውይይቱ ላይ ታድመዋል።
በአጠቃላይ በወላይታ ዞን ሶስት ወረዳዎች እንዲሁም በወላይታ ሶዶ ከተማ ሲካሄድ የሰነበተው የሴቶችና የወጣቶች የክርክርና ውይይት ፕሮግራም ከዳሰሳቸዉ ጭብጥ ሀሳቦች መካከል ለሰላማዊ ፥ ፍትሀዊና ነፃ ምርጫ የሥነ-ምግባርና የዴሞክራሲ እሳቤዎች ሥርፀት ፋይዳ እንዲሁም የሴቶች ተሳትፎና የሥርዓተ ፆታ እኩልነት ለማህበረሰብ እድገት ያለው ሚና የሚሉት ርዕሰ ጉዳዮች በክርክርም በውይይትም በስፋት የተዳሰሱ ሲሆን ወጣቶችም በተጠቀሱት ጭብጦች ላይ የተሻለ ግንዛቤ አግኝተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ይህን መሰሉን ወጣቶች በስፋት ተሳታፊ የሆኑበትን የክርክር መድረክ ሲያግዝ ወጣቶች በአገሪቷ ካለው የሰው ኃይል ቁጥር ከፍተኛውን ድርሻ ከመያዛቸውም ባሻገር የወደፊቱ የሀገሪቷ የለውጥ ተስፋዎች በመሆናቸዉ ተሳትፏቸው በዲሞክራሲ ሥርኣት ግንባታ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ መሆኑን በማመን ነዉ፡፡ ወደፊትም ይህንን መሰል መድረኮችን በመደገፍ ወጣቶች በዲሞክራሲያዊ ምርጫ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤና ተሳትፎ እንዲኖራቸው አተኩሮ የሚሠራ ይሆናል።