የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቦርድ አመራር አባላት ሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ምርጫ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች የምርጫ ሥራዎችን በተመለከተ የመስክ ምልከታና ከባለድርሻ አካላት ጋር ለሁለት ቀናት የቆየ ምክክር አካሄዱ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ6ኛው ዙር የጠቅላላ እና የድጋሚ ምርጫ ባልተካሄደባቸው የቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ የአፋር፣ የሶማሌ እና የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሚያካሂደው ምርጫ የተለያዩ የቅድመ-ምርጫ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑ ይታወቃል። ይህንንም ተከትሎ የመራጮች ምዝገባ ከሚያዚያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በመከናወን ላይ በሚገኝባቸው በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋር እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች የቦርዱ የበላይ ኃላፊዎች የመሥክ ጉብኝት እና ውይይት ከግንቦት 7-8 ቀን 2016 ዓ.ም. አካሂደዋል፡፡
በመስክ ጉብኝቱ በምርጫ ክልሎቹ ላይ እየተከናወነ ያለውን የምርጫ ነክ ሥራዎች ምን እንደሚመስሉ ከመመልከታቸው በተጨማሪ፤ በምርጫ ጣቢያዎቹ በመከናወን ላይ ያለውን የመራጮች ምዝገባ አጠቃላይ ሁነትን የተመለከቱ ሲሆን በየምርጫ ጣቢያዎቹ በሥራ ላይ ከነበሩ ከመራጮች ምዝገባ አስፈጻሚዎች ጋር ውይይት ተደርጓል።
የቦርዱ የበላይ ኃላፊዎች ከላይ በተጠቀሱት አካባቢዎች በአካል በመገኘት የመራጮች ምዝገባ ያለበትን ሁኔታ ከመገምገማቸውም በተጨማሪ፤ በአካባቢው ላይ የመራጮች ትምህርት በመስጠት ከተሰማሩ የሲቪል ማኅበራት፣ በምርጫው ከሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከፀጥታ አካላትና ከክልሎቹ መስተዳድሮች የበላይ ኃላፊዎች ጋር በቦርዱ የክትትልና የቁጥጥር ባለሞያ ቡድን አማካኝነት የቀረቡትን አሁናዊ ሪፖርቶች መሠረት ያደረገ ውይይት አካሂደዋል። የቀረበውንም ሪፖርት መነሻ በማድረግ የተለያዩ ውሳኔዎች ተላልፈዋል፡፡
ከባለድርሻ አካላቱ ጋር በተደረጉት ውይይቶች በቦርዱ የተዘጋጀው አጠቃላይ አሁናዊ የቅድመ ምርጫ ግምገማ ሪፖርት ቀርቦ በጋራ ግምገማ የተደረገበት ሲሆን፤ በዚህም በቀሪ የቅድመ ምርጫ ጊዜያትና በምርጫው ቀን ቦርዱን ጨምሮ በሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊወሠዱ ስለሚገቡ ኃላፊነቶች በዝርዝር ተገልጿል።
የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ሜላት ወርቅ ኃይሉ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በተከታታይ በተደረጉት ውይይቶቹ መዝጊያ ላይ፤ ባለድርሻ አካላቱ ለምርጫው ሂደት መሳካት እያደረጉት ስላለው መልካም አስተዋጽኦ አመስግነው፤ በቀጣይ ያሉት ሥራዎች በሰው ኃይልም ሆነ በቅንጅታዊ አሠራር ከፍተኛ ትብብር የሚጠይቁ በመሆናቸው የባለድርሻ አካላቱ ፈጣን ምላሽና ተሳትፎ ከምን ጊዜውም የበለጠ አስፈላጊ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው አስገንዝበዋል።