Skip to main content

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫና በድኅረ ምርጫ ወቅት በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን በተመለከተ አስጠንቶ ባጠናቀቀው ጥናት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄደ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ እና በድህረ ምርጫ ወቅት በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን በተመለከተ አስጠንቶ ባጠናቀቀው ጥናት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር መጋቢት 12 ቀን 2016 ዓ.ም. ውይይት አካሄደ። ከጥናቱ መጠናቀቅ አስቀድሞ ፤ላለፉት ወራት ጥናቱን መሠረት ያደረጉ ውይይቶች ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ያካሄደ ሲሆን፤ በዚሁ በተጠናቀቀው ጥናት ላይ መጋቢት 12 በተደረገው ውይይት ደግሞ ከዚህ በፊት ያልተሳተፉ ግን የሚመለከታቸው ሲቪል ማኅበራትን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈውበታል።

ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የቦርድ አመራር አባሏ ብዙወርቅ ከተተ ሲሆኑ፤ በንግግራቸውም ቦርዱ ሰባተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ከቀደሙት የተሻለ ለማድረግ የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝና ይህም ጥናት የዛው አካል እንደሆነ ገልጸዋል። ከዚህ በፊት በተደረገው የፖለቲካ ፓርቲዎች የስርዓተ-ፆታ ኦዲት በምርጫ ወቅት የሴቶች ጥቃት ላይ ጥናት እንዲደረግ ተጠቁሞ እንደነበርም አስታውሰዋል። ጥናቱ ሴቶች በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫና በድህረ ምርጫ ወቅት በተለያየ ደረጃ በሚኖራቸው ተሳትፎ እንደ መራጭ፣ እንደ ዕጩ፣ እንደ ታዛቢና እንደ አስፈጻሚ ወዘተ. ስለሚያጋጥሟቸው ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን መዳሰሱን አስረድተዋል። ፆታን መሠረት ያደረጉ የጥቃት ዓይነቶችና መገለጫዎቹ በርካታ ግን ድብቅ እንደመሆናቸው መጠን፤ጥናቱ የራሱ ውስንነቶች ሊኖሩበት እንደሚችልና የተለያዩ የመረጃ መቀበያ አማራጮችን በማካተት ጭምር ወደፊት ተጨማሪ ጥናቶችን ማድረግ ሊያስፈልግ እንደሚችል ገልጸዋል። “በምርጫ ወቅት ፆታዊ ጥቃት” የሚለው ፅንሰ-ሃሳብ በራሱ ለሰው ግር እንደሚል እና ግልፅም ስላልሆነ ተጨማሪ ውይይቶች እና ግንዛቤ እንደሚያስፈልገው ገልፀዋል። በንግግራቸው መጨረሻም ፤ምንም እንኳን ጥናቱ የራሱን የመፍትሔ ሃሳቦች ያስቀመጠ ቢሆንም ከተሳታፊ ባለድርሻ አካላት የሚሰጡ የመፍትሔ ሃሳቦች ከፍተኛ ፋይዳ ስለሚኖራቸው፤ተሳታፊዎች ግብዓት እንዲሰጡ አበረታትተዋል። ይህን ጥናት በማስተባበር የተሳተፉ ባለድርሻ አካላትንም አመስግነዋል።

የውይይቱን የመክፈቻ ንግግር ተከትሎ ጥናቱን ያካሄዱት ባለሞያዎች መሠረት ለገሠና ሸዋዬ ሉሉ ጥናቱን የተመለከተ አጠቃላይ ገለጻ፤ ማለትም ጥናቱ የተከተለውን ሥነ-ዘዴ፣ ሴቶች በኢትዮጵያ ፖለቲካና በምርጫ ያላቸውን ተሳትፎና ተግዳሮቶች፣ በጥናቱ የተካተቱን አካባቢዎች፣ ሥርዓተ ጾታን የተመለከቱ ፖሊሲዎችንና የሕግ ማዕቀፎች ቅኝት፣ እንዲሁም የመፍትሔ ሃሳቦች በባለሞያዎቹ ቀርቦበታል። ጥናቱን በተመለከተም ተሳታፊዎች በቡድን ተከፋፍለው በቦርዱ የሥርዓተ ፆታና ማኅበራዊ አካታችነት ክፍል አስተባባሪነት እንዲወያዩበት የተደረገ ሲሆን፤ የውይይታቸውንም ግኝት በተወካዮቻቸው አማካኝነት እየቀረቡ አስረድተዋል።

Share this post