የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ባዘጋጀው የሴቶች እና የአካል ጉዳተኞች ሩጫ ላይ ተሳትፎ አደረገ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እሁድ መጋቢት 8 ቀን 2016 ዓ.ም. በተካሄደው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የሴቶችና እና የአካል ጉዳተኞች ሩጫ ላይ ተሳትፎ ያደረገ ሲሆን በተለይ የአካል ጉዳተኞች ውድድር ላይ ትኩረት በማድረግ ለአባላቱ ያለውን አጋርነት አጠናክሯል። በዕለቱ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ጀምሮ እስከ ሁለት ተኩል የቀጠለው የሴት አካል ጉዳተኞች የሩጫ ውድድር ‘የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአካል ጉዳተኞች ውድድር' በሚል ስያሜ የተካሄደ ሲሆን በውድድሩ ላይ ከተለያዩ በአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ላይ ከሚሠሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አባላት የተውጣጡ ሴት የአካል ጉዳተኞች ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሚያከናውናቸው በርካታ ተግባራት መካከል ዜጎች በዲሞክራሲያዊ የምርጫ ተሳትፎ የጠራ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እና ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች በሀገሪቱ በሚከናወኑ የተለያዩ ምርጫዎች ላይ ከሌላው ዜጋ ጋር በእኩልነት እንዲሳተፉ የአካታችነት ሥራ መሥራት ይገኙበታል።
ስለዚህም ቦርዱ በዚህ የሩጫ ውድድር የተሳተፈበት ዓላማ የቦርዱን ተግባራት ለማህበረሰቡ ከማስተዋወቅ እና ከማህበረሰቡ ጋር ትስስር ከመፍጠር በተጨማሪ ቦርዱ ከተጋላጭነት ጋር ተያይዞ ትኩረት ለሚያደርግባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች (ሴቶችና አካል ጉዳተኞች) አጋርነቱን የሚያጠናክርበት መድረክ ለመፍጠር ያለመ ነው።